Goolgule.com: ኢህአዴግ ወደ ወታደራዊ አገዛዝ ሊቀየር ይችላል “ህወሃት ብቻ ይነግሳል”

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Mon, 15 Aug 2016 21:23:21 +0200

ኢህአዴግ ወደ ወታደራዊ አገዛዝ ሊቀየር ይችላል

“ህወሃት ብቻ ይነግሳል”
protest 4
 
 

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተካሄደ ያለው የሕዝብ እምቢተኛነት ያሰጋው የኢህአዴግ አገዛዝ በይፋ ወታደራዊ አገዛዝ ለማወጅ ዕቅድ እንዳለው እየተሰማ ነው። ህወሃት ወታደራዊ አገዛዝን ለማወጅ አማራጭ መንገድ የያዘው “አጋር” በሚላቸው ድቃይ ድርጅቶቹ ላይ ያለው እምነት እየተሟጠጠና የቀድሞው ታዛዥነታቸው በመመናመኑ ነው። አገርን ለማዳን በሚል ለአሠራር ያልተመቹትን እያስወገደ ለብቻው ይነግሣል ተብሎ ተነግሯል፡፡

የጎልጉል ዜና አቀባዮች የመረጃ ምንጮቻቸውን ጠቀሰው እንደዘገቡት በኢህአዴግ ስም ህወሃት ራሱ ያደራጃቸው “አቻ ድርጅቶች” አሁን የተነሳበትን የከፋ ተቃውሞ እንደተቀላቀሉበት፣ በነዚሁ ታዛዥ ድርጅቶች አማካይነት የተዘረጋው የጥርነፋና የስለላ ሰንሰለት መፈረካከሱና አባላቱ እንደከዱት ከድምዳሜ ላይ ደርሷል።

በዚህም የተነሳ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ከወጡና ህዝባዊ እምቢተኛነቱ ከሁለቱ ክልሎች ማለትም ከኦሮሚያና ከአማራ ክልል ወደ ሌሎች ከተዛመተ ህወሃት “አጋር” የሚባሉትን ድርጅቶች በይፋ ያፈርሳል፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል፤ ለይስሙላ ይጠቀምበት የነበረውን ሕገመንግሥት ያግዳል፤ የሰዓት ዕላፊ ይደነገጋል፤ ከወታደራዊ ምክርቤቱ (ደርግ) በሚወጣ ትዕዛዝ ብቻ አገሪቱን ማስተዳደር ይጀምራል፤ ይህንንም በማድረግ የነፍጥ አንጋች /ወታደራዊ/ አገዛዝ በማቋቋም የሽግግር ጊዜ ያውጃል። በዚህ ወቅት የተወሰኑ መለሳለሶችና ውጥረት ማርገቢያ ውሳኔዎችን ሊያስተላልፍና ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል፤ ይህም ህወሃትን እንደ አዲስ በማደራጀት የላዕላይ መዋቅሩን እንደያዘ አሁን ካለው ሁኔታ “የተሻለ” የሚያስብል “ጥገናዊ ለውጥ” ማድረግን ይጨምራል፡፡ እንደ መረጃው ምንጮች ከሆነ ይህ ሃሳብ በወታደራዊና ደኅንነት ዙሪያ በርካታ መዋዕለ ንዋይ ባፈሰሱት የህወሃት ለጋሾችና አንጋሾችም ጭምር ተቀባይነት አለው።

ኦሮሚያና አማራ ክልል ህዝብ የራሱን አስተዳደር በማወጅ የገጠርና አነስተኛ ከተሞችን በድንገት ይቆጣጠራል የሚል ስጋት ያለው ህወሃት፣ ከወዲሁ ወታደራዊ አስተዳደር የሚያቋቁምበትንና ህገ መንግስት አፍርሶ አገር በማዳን ሰበብ ያፈቀደውን ርምጃ ለመውሰድ ለራሱ ፈቃድ ለመስጠት ከውሳኔ ላይ መድረሱን ለማወቅ ተsoldiers melesችሏል። የመረጃው ምንጮች አካሄዱን “ባጭሩ ኢህአዴግ ፈርሶ ህወሃት ብቻውን ይነግሳል” ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

ስለጉዳዩ አስተያየት የሰጡ “ይህ አዲስ አይደለም። አሁንም አገሪቱ በወታደራዊ አስተዳደር ነው የምትመራው። ልዩነት ቢኖር አዋጅ የሚያውጁ ከሆነ ብቻ ነው” ይላሉ። አያይዘውም ካሁን በኋላ እንደኩፍኝ ተገልብጦ የወጣውን የህዝብ ቁጣ አሁን ባለው መልኩ ማስቆም የሚቻል እንዳልሆነ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ውሳኔው የሰሩት ግፍና የዘረፉት ሃብት፣ የያዙት እቅድና የተለሙት ህልም ድምር ውጤት ከመሆን እንደማያልፍ ጠቁመዋል።

በኦሮሚያ ለወራት የዘለቀው የመስዋዕትነት ተቃውሞ ኦህዴድ ለመክዳቱ ግልጽ ማስረጃ የሰጠ ሆኗል፡፡ በተለይም በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላቱ በህወሃት እንዲወገዱ ከተደረጉ በኋላ በክልሉ የዘለቀው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ህወሃት ኦሮሚያን በወታደራዊ ዕዝ ሥር እንዲያውል አስገድዶታል፡፡

በይፋ ባይረጋገጥም ሰሞኑን በማኅበራዊ ገጾች የተሰራጨው መረጃ ህወሃት ተመሳሳይ እርምጃ በአማራ ክልል የመውሰድ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በብአዴን ታዛዥነት ለዓመታት በሥራ ላይ ሲውል የነበረው ስለላና ጥርነፋ ከአገልግሎት ውጪ በመሆኑ የአማራን ክልል በወታደራዊ ዕዝ ለመምራት ዕቅድ መነደፉን ይኸው ራሱን “የአማራ ተጋድሎ” በሚል የመረጃ ልውውጥ የሚያደርገው ክፍል በዝርዝር አስታውቋል፡፡

በፌዴራላዊ አወቃቀር የይስሙላ ሥልጣን ለክልሎች እየሠጠ የአገዛዝ ዕድሜውን ያራዘመው ህወሃት አሁን ከገባበት አጣብቂኝ ለመውጣት “አገርን ማዳን” በሚለው ፈሊጥ አዲስ ስሌት መቀመሩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይሰማል፡፡ በመሆኑም በኦሮሚያ ተግባራዊ ከሆነው ጋር ተዳምሮ በአማራ ክልል ለመተግበር እየተወጠነ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር በዓለምአቀፍ ኅብረተሰብ ዘንድ (የሰብዓዊ መብቶች አስጠባቂ ድርጅቶችና የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ) በማያስጠይቅ መልኩ ህወሃት አገሪቱን በፈላጭ ቆራጭ ወታደራዊ የበላይነት እንዲገዛ በር የሚከፍት ይሆናል፡፡

“የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት” በሚል ነገር ግን ጸረ-እኩልነት በሆነ ስልት አናሳው ህወሃት በአገዛዝ የመቀጠሉ ጉዳይ አሳሳቢ ስለሆነበት ኦህዴድ ላይ እንደዘመተው ሰሞኑን ብአዴን ላይም እያመረረ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንጻር የህወሃት ልሣን በሆነው አይጋ ፎረም ላይ ብአዴን መብጠልጠሉ የመጨረሻውን መጀመሪያ እንደሚያመላክት ሃሳብ እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ Exhibits of the Hijack of ANDM by Rotten Neftegnas በሚል ርዕስ የወጣው ጽሁፍ ላይ ስለብአዴን እንዲህ ተብሏል፤

“ብአዴን የራሱ ነፍስ የሌለው ደርግን ለመጣልም በተደረገው ትግልም ብአዴኖቹ ከሞነጫጨሯቸው ጥቂት ግጥሞችና የፍቅር ደብዳቤዎች ውጭ ምንም ሚና የተጫወቱት ነገር አለመኖሩም ገሃድ የወጣ እውነት ነው። እንደውም ብአዴን የህወሃትን ገድል የሚያሳይ ቪዲዮ ሰርቆ ፫፭ኛ ዓመት በዓሉን ሲያከብር በአማራ ቴሌቪዥን ላይ ምንም አይነት ለውጥ ሳያደርግ የራሱ ገድል አስመስሎ አሳይቷል። ብአዴን ይህንን ያደረገው በጦርነቱ ወቅት በባልተቤትነት ይዞት የነበረ አንድ ነጠላ የቪዲዮ ክር እንኳን ስለመኖሩ የሚታውቅ ነገር በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ነው።

“በዚሁ የሰላሳ አምስተኛ አመቱ ክብረ በዓል ላይ ከሃቁ ባፈነገጠ መልኩ ተጣመውና ተጋነው ከቀረቡትጭብጦች መካከል ብአዴን ያለማንም እርዳታ በራሱ ግዜ እራሱን ችሎ የተፈጠረ አስመስሎ ለመዘከር የሄደበት ደረጃ ነው። ይህ ማለት ባጭሩ ብአዴንን ህወሃት የፈጠረው አይደለም ለማለት ተፈልጎ ነው።”

ይህ “ፈጣሪህ ነበርኩ፤ አሁን ደግሞ እንዳትኖር አደርግሃለሁ” የሚለው የህወሃት አስተሳሰብ ግልጽ በሆነ መልኩ በህወሃትና በብአዴን መካከል የተከሰተውን ፍቺ የሚያሳይ ሆኗል፡፡ ህወሃት በዚህ መልኩ “ኢህአዴግ” በሚል ማታለያ ከሰበሰባቸው ድርጅቶች ጋር ፍቺ እየፈጸመ ሄዶ ኢህአዴግን ወደ ወታደራዊ አገዛዝ በመቀየር “ንግሥናውን” ለብቻው ይቆጣጠረዋል፡፡

Received on Mon Aug 15 2016 - 14:02:25 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved