Goolgule.com: “ጸጥታ አስከባሪው” ህወሃት/ኢህአዴግ ጸጥታው ሊገመገም ነው

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Thu, 11 Aug 2016 21:54:17 +0200

“ጸጥታ አስከባሪው” ህወሃት/ኢህአዴግ ጸጥታው ሊገመገም ነው

የህወሃት ጄኔራሎች “የኢትዮጵያን ሰላም ለማከበር” ይመደባሉ?!
un zeid
 

ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ በሚመስል ሁኔታ ኢትዮጵያ በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን ዓለምአቀፋዊ ዕውቅና ያገኘች አስመስሎ የሚያወራው ህወሃት “ጸጥታ አስከባሪ ነኝ” እያለ በአፍሪካ ሳይጠሩት አለሁ የሚለውን ያህል አሁን ደግሞ በተራው በአገር ውስጥ ህዝብን ጸጥታ በመንሳት ሊገመገም መሆኑ ተነገረ፡፡ “በኢትዮጵያ ሰላም ለማስከበር በሚል የህወሃት ጄኔራሎች የተባበሩት መንግሥታትን ምደባ እየጠየቁ ነው” በማለት አስተያየት ሰጪዎች ተሳልቀዋል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክርቤት ድምጽ የማትሰጥ አባል ሆና መመረጧ የህዳሴው ውጤት ነው፤ የመለስ ራዕይ ተግባራዊነት ነው፤ … በማለት ከፍተኛ ዲስኩር የነፋው፤ ከበሮ የደለቀው ህወሃት “ህዝብን ጸጥታ ነስተሃል” ተብሎ በተባበሩት መንግሥታት የምርመራ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ በንጉሡ ዘመን እንዲሁም በደርግ ጊዜ የጸጥታው ም/ቤት አባል በመሆን ማገልገሏ እንዳይነገር ብዙ ፕሮፓጋንዳ የሠራው ህወሃት የጸጥታው ምክርቤት የአባልነት ዘመኑ በ2017 ከመጀመሩ በፊት ይህ የገጠመው ችግር ያልታሰበ ዱብዕዳ ሆኖበታል፡፡ በመጪዎቹ የአውሮጳውያን ዓመት በጸጥታው ም/ቤት ወንበር ላይ ተቀምጦ በኤርትራና በሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ከማዕቀብ ጀምሮ ያሻውን ዓይነት ውሳኔ እንዲተላለፍ ዝግጅት ያደረገው ህወሃት/ኢህአዴግ የተመኘውን ወንበር በፎቶ እንዳየው በዚያው ሊቀር እንደሚችል አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ethiopia-security-council

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ዘዒድ ራድ አል ሁሴን ጄኔቭ ስዊትዘርላንድ በሚገኘው ጽ/ቤታቸው ለሬውተርስ በሰጡት መግለጫ ህወሃት/ኢህአዴግ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሰላማዊ ሰልፍ በወጣው ህዝብ ላይ ጥይት መተኮሱና 90 ሰልፈኞችን መግደሉ መረጃዎች ደርሰውናል ብለዋል፡፡ ይህንን ለማረጋገጥም ምርመራ ማድረግ የግድ እንደሆነ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽነሩን የጠቀሰው የዜናው ዘገባ “የኢትዮጵያ መንግሥት ታዛቢዎች ምርመራ እንዲያደርጉ መፍቀድ አለበት” ብሏል፡፡

በሰላም ሰልፍ የወጡና የታሰሩ በሙሉ መለቀቅ አለባቸው ያሉት ኮሚሽነር ዘዒድ መርማሪዎች በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ሄደው ምርመራቸውን ማካሄድ እንዲችሉ ከህወሃት/ኢህአዴግ ሹሞች ጋር ንግግር መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ከኢሳያስ አፈወርቅ ተቃዋሚዎች ጋር በማበር የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ራፖርተር ዘገባ እንዲወጣና ኤርትራ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጉድጓድ ሲቆፍር የነበረው ህወሃት የራሱን መቀበሪያ ራሱ ቆፍሯል በማለት አስተያየት ሰጪ ለጎልጉል ተናግረዋል፡፡ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በተደጋጋሚ በበቂ ማስረጃ ገዳይነቱን የመሰከሩለት ህወሃት/ኢህአዴግ፤ በዚህ የተባበሩት መንግሥታት ምርመራ ወንጀለኛ ሆኖ እንደሚገኝ ጥርጥር እንደሌላቸው በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ ይናገራሉ፡፡

በአፍሪካ የተለያዩ አገራት የሰላም አስጠባቂ በመሆን ባልተጠራበት ሁሉ ወታደር እየላከ “ሰላም አስከባሪ ነኝ” ሲል የኖረው ህወሃት ሰላመ-ቢስ ብቻ ሳይሆን ጸጥታ አደፍራሽ መሆኑ ይፋ የሚደረግበት ጊዜ ላይ ነን የሚሉ ወገኖች ህወሃት የሻዕቢያን መቀበሪያ ሲያዘጋጅ ራሱ ሊቀበርበት ነው ብለዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዘገባ ይፋ በሚሆንበት ጊዜ ሰላማዊ ሰዎችን በመግደልና በማስገደል እጃቸው ያለበትን ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ዘገባው በማስረጃ ሰነድነት እንዲያዝ ከማድረግ ባለፈ ጥፋተኞቹን ለፍርድ የሚቀርቡበትንም አካሄድ ያመቻቻል፡፡

ያለ ዕውቀታቸውና ያለ ወታደራዊ ብቃታቸው ለሥራ ማመልከቻ እንዲረዳቸው የጄኔራልነት ሹመት የተጎናጸፉት የህወሃት ወታደራዊ ሹሞችና የቀድሞ የጦር ኃላፊዎች በሌላ የአፍሪካ አገር እንደለመዱት “በኢትዮጵያ ሰላም የለም፤ ጸጥታ ደፍርሷል፤ … የኢትዮጵያን ጸጥታ እናስከብራለን” በማለት የቅጥር ማመልከቻ እያቀረቡና ምደባ እየጠየቁ ይሆናል ሲሉ የህወሃትን ጠባብነትና ጭፍንነት የሚያውቁ ስላቃዊ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡

ከዕውቀት ጋር ጠበኛ የሆነውና በተለይ የቁጥር ስሌት ሰለባ የሆነው ህወሃት በቁጥጥሩ ሥር ባደረገው ሚዲያ በአማራና በኦሮሞ ከተሞች የወጡትን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ሰላማዊ ሰልፈኞች “ጥቂት ጸረ ሰላም ኃይሎች” ብሎ በመሰየም ተቃውሞውን በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ማለቱ ለግድያው ራሱ ኃላፊነት ስለመውሰዱ ምስክርነት የሰጠበት ሆኖ ለኮሚሽኑ እንደ ቀዳሚ ግብዓት እንደሚወሰድ ታውቋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ምርመራውን እንዲደርግና በህወሃት ሹሞች እንዳይታለል በተለይ በዳያስፖራ ያለው ኢትዮጵያዊ በኮሚሽኑ ላይ ግፊት እንዲያደርግ ተጠይቋል፡፡

Received on Thu Aug 11 2016 - 14:33:23 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved