Ethsat.com: በሚኦ ወረዳ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ዋለ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 27 Jul 2016 21:58:31 +0200

በሚኦ ወረዳ የተጀመረው  ህዝባዊ ተቃውሞ ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ዋለ

July 27, 2016

Watch.

http://video.ethsat.com/?p=26336

ሐምሌ  ፳ ( ሀያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቦረና ዞን በሚኦ ወረዳ ሂዲ ሎላ ከተማ በተነሳው ህዝባዊ አመጽ አንድ ሰው ሲገደል ሁለት ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች  “ሞያሌ ከተማ በሁለት ክልሎች መተዳደሩ ተገቢ ባለመሆኑ ወደ ኦሮምያ ክልል ይጠቃለል፣ ዩኒቨርስቲ ይከፈትልን፣ ፍትህ ይሰጠን፣ ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችን ይከበሩልን፣ የወያኔን የመከፋፈል ፖሊሲ እንቃወማለን፣ ይህ መንግስት አይወክለንም፣ አያስተዳድረንም “ የሚሉ እና ሌሎችንም አካባቢዊ ጥያቄዎች አንስተዋል። የአሁኑ ሰልፍ ባለፈው ሳምንት በያቤሎ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ የተዘጋጀ ነው። በያቤሎ ተካሄዶ በነበረው ሰልፍ የወረዳው ባለስልጣናት በአገር ሽማግሌዎች በኩል በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ መልስ እንደሚሰጡ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን መልስ አልሰጡም።  በዛሬው አመጽ ቃባር ቀርባቶ የተባለ ሰው ሲገደል፣ ሌሎች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። ትናንት 6 ሰዎች ተይዘው መታሰራቸውን የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በምስራቅ ሸዋ ዞን ከሞጆ ከተማ 5 ኪ/ሜ ርቀት ላይ በምትገኘዋ ኤጀርሳ ከተማ ህዝቡ በድንጋይ መንገድ በመዝጋት ተቃውሞ በማስነሳቱ ወደ ሻሸሜ የሚደረግ ጉዞ ተቋርጦ መዋሉ ታውቋል። በኦሮምያ እንደገና የተጀመረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር ገዢው ፓርቲ የአጋዚ ሰራዊት አባላትን በስፋት እያሰማራ ነው። የፌደራል ፖሊስ አባላት አገሪቱን በሃይል መቆጣጠር እንደማይቻልና ፖለቲካ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ እየወተወቱ ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የፌደራል ፖሊስ ልብስ በማልበስ ተቃውሞዎችን በሃይል ለመጨፍለቅ መወሰኑን ምንጮች ይገልጻሉ።

******************************************************************************************

የገዢው ፓርቲ ሹሞች በስብሰባ አዳራሽ ላይ የጠየቁትን ይቅርታ በመገናኛ ብዙሃን ለመድገም አልደፈሩም ተባለ

July 27, 2016

ሐምሌ  ፳ ( ሀያ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር የተጀመረውን ህዝባዊ አመጽ  ተከትሎ ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የገባው የ ህወሃት /ኢህአዴግ  አመራርና ክልሉን የሚያስተዳድረው ብአዴን፣ እንቅስቃሴውን ለማብረድ ከትናንት በስቲያ ጎንደር ከተማ ውስጥ ከተወሰኑ የወልቃይት የአማራ ማንነት የኮሚቴ አባላት፣ ከታዋቂ ሰዎችና ከአገር ሽምጋሌዎች ጋር ያደረገው ስብሰባ ያለውጤት ተበትኗል።

ነባሩ የብአዴን ታጋይ እና የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ በረከት ስምዖን፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ገዱ አንዳርጋቸውና ምክትላቸው አቶ ብናልፍ አንዷለም ስብሰባውን መርተዋል። በስብሰባው ላይ የተሳተፉት ሰዎች ብአዴን በህወሃት እያስጠቃቸው መሆኑን የተለያዩ መረጃዎችን በማቅርብ ተናግረዋል።

ህወሃት ድፍረት በተሞላበት መንገድ በክልላችን ገብቶ ሰዎችን አፍኖ ለመውሰድ ያደረገውን ሙከራ በመቃወማችን ሽብረተኞች ተብለን በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ተብጠልጥለናል በማለት የተናገሩት ተሳታፊዎች፣ ይህም ዘገባ በይፋ እንዲስተባበልላቸው ጠይቀዋል። ዘገባውን ስህተት መሆኑን የገለጹት አቶ በረከት፣ ተሰብሳቢውን ይቅርታ ቢጠይቁም፣ ተሰብሳቢዎች ግን በአደባባይ እንደተዘለፍን በአደባባይ ይቅርታ እንጠየቅ የሚል አቋም አንጸባርቀዋል።

ሃምሌ 5፣ 2006 ዓም ታፍነው የተወሰዱ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት የኮሚቴ አባላት እንዲለቀቁ፣ በክልሉ የሚካሄደው ህገወጥ አፈና እንዲቆም፣ ከወልቃይት ጠገዴ ጋር በተያያዘ የታሰሩት ዜጎች እንዲፈቱ የሚሉና በርካታ ጥያቄዎች፣ ትችቶችና አስተያየቶች ቀርበዋል። መድረኩን የመሩት የአብዴን መሪዎች ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በቂ መልስ ሳይሰጡና ተሰብሰባዊውን ሳያረኩ ስብሰባው ተጠናቋል።

በሌላ በኩል የቀድሞዋ የህወሃት ታጋይ የነበሩት ታጋይ ርስቴ መብራቱ በኢሳት የሰጡት ቃለምልልስ በአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ ተቀባይነት ማገኘቱና መነቃቃት መፍጠሩ ታውቋል። ግለሰቡዋን በቅርበት የሚያውቋት ሰዎች እንደተናገሩት ታጋይ ርስቴ የወልቃይትን ህዝብ ከጨፈጨፈው ህወሃት ጎን ቆማ በመታገሏ የአካባቢው ህዝብ አዝኖባት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በቃለምምልሷ ህዝቡን መካሱዋን እና ከፍተኛ የመነቃቃት ስሜት መፍጠሯን ተናግረዋል።

ታጋይ ርስቴ ”ከህወሀት ጎን ተሰልፌ የተዋጋሁት ለህዝቤ ባርነትን ለማምጣት አልነበረም። ማንነቴ ተቀይሮ ሌላ ለመሆን አልነበረም። ይጸጽተኛል። ለህዝቤ ባርነትን ካመጣ ስርዓት ጋር ተሰልፌ የልጅነት እድሜዬን መጨረሴ ይቆጨኛል። የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ማለቷ ይታወቃል።

የአካባቢው ህዝብ  የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ባለቤትና የኢፈርት ስራ አስኪያጅ አዜብ መስፍንም በተመሳሳይ መንገድ ወልቃይት ጠገዴ አማራ እንጅ ትግሬ አለመሆኑን እንድትናገርና የተሰራውን ደባ  እንደ ታጋይ ርስቴ ታጋልጣላች ወደ ማንነቷም ትመለሳለች ብሎ እየጠበቀ ነው። ወ/ሮ አዜብ ቀድሞ ወልቃይት ጠገዴ ትግሬ ነው የሚል አቋም ሲያራምዱ ከቆዩ በሁዋላ፣ ካለፉት ሁለት አመታት ጀምሮ ግን ይዘውት በነበረው የተሳሳተ አቋም እያዘኑ እንደሚገኙና የኮሚቴው አባላትንም ሆነ ጥያቄውን የሚያቀረቡ ሰዎችን መተቸትና መንቀፍ ማቆማቸውን ከቤተሰቦቻቸው አካባቢ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በእናታቸውም በአባታቸውም የወልቃይት ተወላጅ የሆኑት ወ/ሮ አዜብ በድፍረት ወጥተው አቋማቸውን ለህዝብ ግልጽ ባያደርጉም ከፍተኛ ብዥታ ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።

Received on Wed Jul 27 2016 - 14:37:35 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved