Zehabesha.com: የምእራብ ኣርሲውን የህዝብ ተቃውሞ ከተቀረው የኦሮምያ ኣካባቢ ለይቶ ለማሳየትና ለማስፈራራት የተፈለገው የገዛ የስርኣቱ ታጣቂ ኣካል ኣፈሙዙን ኣዙሮ የኣጋዚን ጥጋብ በማስተንፈሱ ብቻ ነው

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Fri, 26 Feb 2016 16:28:48 +0100

ከ ቦሩ በራቃ

Minilik Salsawi's photo.ኣራተኛ ወሩን የያዘውን የሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ ኣልገዛም ባይነት ንቅናቄ እንደለመደው ኣፍኖ ማስቀረት ያቃተው ህወሃት ወያኔ ለንቅናቄው የተለያዩ ስሞችን እየሰጠ ለማናናቅ የሚያደርገውን ጥረት ቀጥሏል። በተለይም ህዝባዊ ቁጣው በሃይል በገነፈለባቸው ኣካባቢዎች የተለመደው የስርኣቱ ያረጀና ያሰለቸ ዉንጀላ ተደጋግሞ ይታያል። ህዝብ ለሚጠይቃቸው ቀጥተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ቀጥተኛ ምላሽ መስጠት የማይፈልገው ኣምባገነኑ ቡድን የህዝብን ጥያቄ የጥቂት ወገኖች ኢፍትሃዊ ፍላጎት ኣስመስሎ ለመምታት ከማለም የቦዘነበት ጊዜ የለም።

እንደ ሰደድ እሳት መላውን ኦሮምያን በማዳረስ ተፋፍሞ በቀጠለው በዚህ የኦሮሞ ህዝብ ተቃውሞ ውስጥ ምእራብ ኣርሲን ልዩ ያደረገው ምንድነው? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው። ምላሹም እንደየሰዉ ኣመለካከት ሊለያይ ይችላል። ሃቀኛው ምላሽ ግን ግልፅ ነው። በዚህ ጽሁፍ ኣርእስትነት ለመግለጽ እንደተሞከረው ጉዳዩ በዋናነት ከኣጋዚ መመታት ጋር የተያያዘ ነው። ወያኔዎቹ በእጅጉ የሚመኩበት ነፍሰ-ገዳዩ ቅልብ ጦራቸው ኣግኣዚ በ24 ኣመቱ የስርኣቱ ኣገዛዝ ታሪክ ውስጥ የተዋረደበት ቦታ ቢኖር ምእራብ ኣርሲ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል። ህይወቱን ሙሉ መግደል እንጂ ተገድሎ የማያውቀው ኣሸባሪው የኣጋዚ ጦር ኣርሲ ላይ ተደቁሷል። በኣንድ ቀን ብቻ 11 ኣባላቱ የተቆጣው ህዝብ በወሰደበት እርምጃ ተገድሏል። ከተገደሉት የኣጋዚ ጦር ኣባላት ኣንዳንዶቹ ኣስከሬናቸው መሬት ላይ ሲጎተት የሚያሳዩ ምስሎችም በየማህበራዊ ሚዲያዎች ተለቀው ታይተዋል።

ታሪኩን ለየት የሚያደረገው ታድያ እንደ መልኣከ-ሞት የሚታዩትና የሚፈሩት እነዚህ ገዳዮች መገደላቸው ብቻ ሳይሆን እርምጃውን የወሰደባቸው የገዛ የስርኣቱ ታጣቂ ኣካል የሆነው የኦሮምያ ፖሊስ መሆኑ ነው። የኦሮምያ ፖሊስ ኣባላት ኣርሲ ላይ ታሪካዊ ጀብዱ በመስራት ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ ያደረጋቸው ደግሞ ሰው በላው ኣጋዚ ቡድን ባልታጠቀ ህዝብ ላይ የሚያደረሰው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ነው። ወያኔዎች እንደ ኣለንጋ ተጠቅመው ኦሮሞን ሊገርፉት ያሰለጠኑት የኦሮምያ ፖሊስ ኣባሎች ትእግስታቸው ሞልቶ ፈሰሰና በኦሮሞ ትግል ታሪክ መዝገብ ውስጥ ስማቸውን በደማቸው ፅፈው ህያው ክብር ተጎናጸፉ። ወያኔ ይህ ይሆናል ብሎ የገመተ ኣይመስልም። እናም ዜናውን ሲሰማ በእጅጉ ደንግጦ ተወራጨ። የኣርሲውን የኦሮሞ ህዝብ ኣመፅም ከተቀረው የኦሮምያ ህዝብ ኣመፅ ለይቶ ለመምታት ሌላ ስም ሊለጥፍበት ተገደደ። በጥድፊያ የታዩትም ሁለት የተለመዱ ኣሰልቺ ስልቶች ናቸው።

የመጀመሪያው የተለመደውን የሃይማኖት ልዩነት ካርድ መምዘዝ ነበር። ይህንን የቀቢጸ-ተስፋነት ጥረቱንም በጥፋት መልክተኞቹ ኣማካኝነት ለማስፈፀም ሞከረ። ኣብያተ-ክርስቲያናትና መስጊዶችን በቅጥረኞቹ ኣማካኝነት በማቃጠል ድርጊቱን ኣደገኛ ጠላቶቼ ብሎ በሚፈራቸው ወገኖች ላይ ኣላክኮ መምታት የመጀመሪያው እርምጃው ነበር። ከዚሁ ጎን ለጎንም በብሄር ኦሮሞ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ የሽብር ድርጊትም ኣስፈጽሟል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ህዝባዊ ንቅናቄውን በጸረ-ክርስቲያንነት ለመፈረጅ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። ኣላማውም ግልጽ ነው። የኦሮሞን ፍትሃዊ ትግል በሙስሊም ኣክራሪነት ፈርጆ ህዝበ ክርስቲያኑን ሁሉ ከጎኑ ለማስቆም ነበር ምኞቱ። ቱልቱላዎቹ የስርኣቱ ተቀጣሪ ሚድያዎችም ይህንኑ የሞኝ ጩሄት ባንድ ጥሩምባ ኣስተጋቡ። የሃሰት ውንጀላው በችኮላ የተቀነባበረ በመሆኑም በኣስቂኝ ስህተቶች የተሞላ ነበር። ከኣመታት በፊት ግብፅ ኣገር የተቃጠለውን ቤተ ክርስቲያን ምስል በመጠቀም ሻሸመኔ ላይ በኦሮሞ ታጋዮች የተቃጠለ ኣስመስለው በማህበራዊ ሚድያና በየብሎጎቻቸው ላይ ለቀቁት። ከጥቂት ኣመታት በፊት ደቡብ ክልል ሆሳእና ላይ ተቃጥሎ የነበረው ቤተ ክርስቲያን ምስልም በዚህ ድራማ ውስጥ ጥቅም ላይ ሲውል ኣይተናል። በተለይም የግብፁን ቤተ ክርስቲያን መቃጠልና የኣርሲውን ጉዳይ ሃራምባና ቆቦነት ቶሎ ለይተው የነቁባቸው ወገኖች ቶሎ ሳቁባቸው። መጀመሪያ ላይ ምስሉን ሲያዩት ጥርጣሬ የገባቸው ብልሆች ደግሞ ወዲያው ‘ጉግል’ ኣደረጉትና ሃቁን ደረሱበት። እውነት መስሎኣቸው በድንጋጤ ያማተቡ የዋሆችም በርግጥ ቁጥራቸው ቀላል ኣልነበረም።

እዚህ ጋር ወያኔዎችም ሆነ ኣንዳንድ ያለኣግባብ ግራ የተጋቡ ወገኖች ከስህተታቸው መማር የተሳናቸው ኣልያም እያወቁ የኦሮሞን ህዝብ ትግል በጠላትነትና በጥርጣሬ መመልከትን የፈለጉ ሁሉ መረዳት ያለባቸው ሃቅ ኣለ። የኦሮሞን ህዝብ ጸረ-ክርስትና ያደረገው ማን ነው? እነርሱን ደግሞ ብቸኛ የክርስትና ሃይማኖት ተሟጋችና ተቆርቁዋሪ ያላቸውስ ማን ነው? የክርስትና ሃይማኖት ኢትዮጵያ ውስጥ ኣሁን የያዘውን ትልቅ ቁጥር ኣንዲይዝ ከፍተኛ ኣስተዋጽኦ ያደረገውኮ የክርስቲያን ኦሮሞው ቁጥር ነው። እስካሁን ኣራተኛ ወሩን በያዘው የኦሮሞ ህዝብ ንቅናቄ ውስጥ ኣንኩዋን የተሰዉት ከ500 በላይ ከሚሆኑት የኦሮሞ ጀግኖች መካከል ግማሽ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት በክርስቲያናዊ ህግ መሰረት ፍትሃት ተደርጎላቸው ክርስቲያናዊ ስርኣተ ቀብር እንደተፈፀመላቸው ኣያውቁምን? ይህንን ሃቅ ረስተውት ነው ወይስ እያወቁት ኣያውቁም የሚሉትን ወገን ማጃጃል ፈልገው ነው? ወይስ ኦሮሞውን በሃይማኖት ልዩነት ኣቃቅረን በመከፋፈል ኣስፈሪውን የኣንድነት ሃይሉን ድል እናደርጋለን ብለው ኣልመው ነው?

የሆነውስ ሆኖ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ቤተ ክርስቲያንም ሆነ መስጊድ ላይ የሚያነጣጥርበት ምንም ኣይነት ኣሳማኝ ምክንያት የለም ሊኖረው ኣይችልም። ሁለቱም ቤተ እምነቶች የኦሮሞ ናቸው። ኦሮሞም የሁለቱ ቤተ እምነቶች ነው። ኦሮሞን በድፍን ሙስሊምነት ፈርጆ በክርስቲያን ላይ ኣነሳሳለሁ ብሎ ማለም ከንቱ ጅልነት ብቻ ሳይሆን ሃጢያተኝነትም ጭምር ነው። በኣንጻሩ ደግሞ ኦሮሞን በክርስቲያንነት ፈርጆ ጸረ ሙስሊም ኣስመስሎ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ለማስቆጣት የሚደረግ ሙከራ ካለም ራስን ማታለል ብቻ ነው የሚሆነው። ገና ከጠዋቱ ኦሮሞ ሲታደል ከማናቸውም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በተሻለ መልኩ ብዙሃ-ሃይማኖት (multi religious) ህዝብ ነው። የኦሮሞ ህዝብ ትግል በታላላቅ ቄሶችና ፓስተሮች እንዲሁም በኣሊም ሼኾችና ቃሉዎች የጋራ ኣላማና ቁርጠኝነት ኣንድ ብሎ መራመድ የጀመረ ትግል ነው።

ወያኔዎቹ ህዝብንና ኣለምን ለማታለል የከጀሉበት ይህ ጥረታቸው ይበልጥ ኣስቂኝ የሚሆነው ደግሞ ሻሸመኔና ኣካባቢው ላይ በማነጣጠሩ ነው። የዚህ ኣካባቢ የኦሮሞ ህዝብ በቤተሰብ ኣባላት ሳይቀር የተለያዩ እምነቶችን የሚከተልና በሃይማኖት መቻቻል ምናልባትም ከወሎ ቀጥሎ ኢትዮጵያ ውስጥ በምሳሌነቱ መጠቀስ የሚችል ህዝብ ነው። በዚህ ኣካባቢ መመኪያዬ የሚለው የኣጋዚ ጦሩን ጥጋብ የማስተንፈስ ድፍረትና ኣቅም ያላቸው ውድ የኦሮሞ ልጆች ብቅ በማለታቸው በእጅጉ የተደናበረው ወያኔ ያጋጠመውን ሽንፈትና ውርደት ለመሸፋፈን ሲል ‘የታጠቀ የውጭ ሃይል’ በኣካባቢው ታይቷል፣ የህዝብ ጥያቄን ለመጥለፍ ሞክሯል ሲል ቅዠቱን ኣሰማ።

የሃይማኖት ልዩነት ካርዱም ኣልሰራለት ከማለቱ ጋር ተያይዞ ኣሁን ደግሞ ፊቱን እንደተለመደው ወደ መከረኛው የኤርትራ መንግስት ኣዞረ። ምእራብ ኣርሲ ውስጥ ላጋጠመው ሽንፈት የኤርትራን መንግስት ተጠያቂ ማድረግ ሁለት ኣስነዋሪ መልእክቶችን ኣዝሎ ብቅ ብሏል። የመጀመሪያው ሁሌም እንደተለመደው ስርኣቱ ለኦሮሞ ህዝብ ትግል ያለውን ንቀት የሚገልጽበት መንገድ ነው። በስርኣቱ ኣካላት ላይ ሃይለኛ ምት በተሰነዘረበት የኦሮምያ ኣካባቢ ሁሉ እርምጃው የሚላከከው በኤርትራ መንግስት ላይ ነው። ይህ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ያለ ባእድ ኣካል ድጋፍ ራሱን ችሎ በራሱ ልጆች ስትራቴጂ፣ ኣቅምና ጀግንነት ምንም ኣይነት እርምጃ በስርኣቱ ላይ መውሰድ የማይችል ኮሳሳ ህዝብ ኣድርጎ እንደመዝለፍ ነው። ለተነሳው ህዝባዊ ጥያቄም ጆሮ ለመክፈት ዝግጁ ኣለመሆኑን ይጠቁማል። ሃይለኛ ቡጢ የሚያርፍበት ከሆነ ሁሌም የኤርትራ መንግስት እጅ ኣለበት የሚል መልእክት ማስተላለፍ ይቀናቸዋል። ይህም ውንጀላም ኣውቀውም ይሁን ሳያውቁት ጠላታችን ለሚሉት የኤርትራ መንግስት ተጨማሪ ክብርና ዝና ማጎናፀፊያነት እየዋለ ስለመሆኑ ልብ እንላለን።

ለምእራብ ኣርሲው ጉዳይ የኤርትራን መንግስት ተጠያቂ በማድረግ ለማስተላለፍ የተፈለገው ሁለተኛው መልእክት በኣይነቱ ኣዲስና የመጀመሪያው ሊባል የሚችል ነው። እሱም ኦነግን የሚመለከትና እርስ በራሱ የሚጣረዝ ነው። የወያኔ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊው ጌታቸው ሬዳ ይህንን ኣስመልክተው ለውጭ ሚድያዎች ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ቃል በቃል ‘የኤርትራ መንግስት ኣስመራ ውስጥ ተቆርጠው ከቀሩት የኦነግ ኣባላት ጋር ብቻ ሳይሆን ግንቦት7 ከመሰሉ ሃይሎችም ጋር ይሰራል።’ ብለዋል። እዚህ ጋር ነው እንግዲህ ግራ የሚያጋባውና እርስ በራሱ የሚጋጭ ኣባባል የሰማነው። ባንድ በኩል የኦነግ ኣስመራ ውስጥ ተቆርጦ መቅረት ተነግሮናል። በሌላ በኩል ደግሞ የኤርትራ መንግስት ኣስመራ ውስጥ ‘ቆርጦ ካስቀረው’ ኦነግ ጋር በኣርሲው ጉዳይ እጁን ኣስገብቷል ከተባለ ኦነግ ኣስመራ ውስጥ ‘ተቆርጦ ቀርቷል’ የተባለው ትክክል ኣይደለም ማለት ነው። ኣስመራ ውስጥ ‘ተቆርጦ የቀረ’ ሃይል ኣርሲ ድረስ ክንዱን መሰንዘር ኣይችልምና።

ይቺ ‘ተቆርጦ መቅረት’ የምትለው ሃረግ ያለ ምክንያት የተቀመጠችም ኣይደለችም። ኦሮሞን መሪ ድርጅት ኣልባ ኣድርጎ ተስፋ ለማስቆረጥ ዛሬም ከንቱ ድካም እንዳለቀቃቸው ታመላክታለች። የኦሮሞ ህዝብ በራሱ ሃይል ተነስቶ የራሱ ኣገር ላይ ታሪክ ሲሰራ 4 ወር ሙሉ ባይናቸው እያዩ ዛሬም ያረጀ ያፈጀ የኤርትራ ተረት ተረታቸውን ያወራሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለኦነግና ለግንቦት7 ወያኔዎች የሰጡት ኣገላለጽ ፈገግ የሚያሰኝ ነው። ኦነግ ኣስመራ ውስጥ ተቆርጦ የቀረና ግንቦት ሰባት ግን እንደፈለገ እየወጣ የሚገባ ኣይነት ያህል ልዩነት እንዳላቸው ሊነግሩን ሞክረዋል። እንደዛ ከተባለም ሌላ ከራሱ ጋር የሚጋጭ ሃሳብ እናያለን። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ትግሉ የኣለምን ትኩረት መሳብ በቻለ ደረጃ ኣየተፋፋመ ያለው በኦሮምያ ነው። እንዲህ ከሆነ ደግሞ እንደልቡ ወጥቶ የሚገባው ግንቦት7 ከፍተኛ ድጋፍ ባለው የኢትዮጵያ ኣካባቢዎች መስራት ያልቻለውን የፖለቲካ ስራ ‘ኣስመራ ውስጥ ተቆርጦ የቀረው’ ኦነግ የድጋፍ መሰረቱ በሆነው ኦሮምያ ውስጥ መስራት ችሏል እንደማለት ይመስላል። ወይም ደግሞ በኣርሲው ጉዳይ የግንቦት7 እጅ ኣለበት የሚል እንደምታም ኣለው።

ለነገሩ ከድሮም ጀምሮ ኦሮምያ ውስጥ ህዝባዊ ቁጣ በፈነዳ ቁጥር የኦነግና የኤርትራ መንግስት ስም ሲነሳ ነው የኖረው። የዘንድሮውን የተለየ የሚያደርገው ግን ኣንደኛ ኦነግ ኣስመራ ውስጥ ‘ተቆርጦ መቅረቱ’ና ሁለተኛው ደግሞ ድርጅቱና የኤርትራ መንግስት በሁሉም የኦሮምያ ኣካባቢዎች የተነሳውን ተቃውሞ ችላ ብለው በኣርሲው ጉዳይ ብቻ እጃቸውን ማስገባታቸው ነው። የኤርትራ መንግስትም ሆነ ‘ኣስመራ ውስጥ ተቆርጦ ቀርቷል’ የተባለው ኦነግ ለኦሮምያው ኣመጽ ተጠያቂዎች ከተባሉ መሬት ኣንቀጥቅጥ ኣመፆች በታዩባቸው በምእራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምእራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ሃረርጌ፣ ምእራብ ሃረርጌ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ምእራብ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ጉጂ፣ ቦረናና ሌሎችም ኣካባቢዎች ይልቅ በምእራብ ኣርሲው ጉዳይ ብቻ የተለየ እጅ ማስገባት የፈለጉበትን ምክንያት ወያኔዎቹ ለማብራራት ኣልፈለጉም። ጉዳዩ የኣጋዚ ጦር በህዝብ ክንድ መደፈሩ ነውና ይህን ደግሞ ለማብራራት ያሳፍራልና። ትልቁ ማብራሪያቸው ሆኖ የቀረበው ‘የታጠቀ የውጭ ሃይል’ በኣካባቢው ቤተ ክርስቲያን ኣቃጠለ፣ የመንግስትና የግለሰብ ንብረቶችን ኣወደመ፣ ኦሮሞ ያልሆኑ ግለሰቦችን ለይቶ ኣጠቃ፣ ህጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ሰርጎ ገባ ወዘተ የሚሉ ተልካሻና የጉዳዩን ኣስኩዋል መዳሰስ የማይፈልጉ ምክንያቶች ናቸው።

የዚህ ሁሉ ግራ መጋባት መንስኤ ደግሞ ከላይ እንደተጠቀሰው የኣጋዚው ‘ኣይበገሬ’ ጦራቸው ኣርሲ ውስጥ ተድቁሶ መዋረድ ነው። ህዝብ ኣምርሮ ከተነሳ ነፍሰ ገዳዩን ኣጋዚን መመከት ብቻ ሳይሆን ኣከርካሪውን እየመታ ማጥቃትም እንደሚችል በተግባር ሲያሳያቸው ኣምነው መቀበል ኣቃታቸው። ህዝብን ይንቃሉና የህዝብን ኣቅም ኣምነው መቀበል ይከብዳቸዋል። ክቡር መስዋእትነት እየተከፈለበት ያለውን የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከኣስመራ ጋር ለማያያዝ መሞከር የፖለቲካ ስካር ብቻ ነው መሆን የሚችለው።

የኣርሲ ወገኖቻችን ለተቀሩት የኦሮምያ ኣካባቢ የትግሉ ኣካላት ሁሉ በተለይም የመንግስት መሳሪያ ለታጠቁት የኦሮሞ ተወላጆች ጊዜ የማይሽረው ታሪካዊ የጀግንነት ምሳሌ ሆነዋል። ይህም የስርኣቱን የመጨረሻ መጀመሪያ ያመላከተ ነው። ወያኔን ኣሳብዶት የባጥ የቆጡን እንዲዘላብድ ያስገደደውም ይሄው ነው። ኣርሲ ውስጥ ‘ኣይበገሬ’ ተብዬውን የኣጋዚ ገዳይ ጦር የደፈረው ኣይነት እርምጃ በተቀሩት የኦሮምያ ኣካባቢዎች ቢደገምና በሌላውም የጭቆናው ገፈት ቀማሽ ክልሎች ዘንድም ቢሰለስ ወያኔ የመውደቂያው ወይም የመንበርከኪያው ደወል ይደወላል። ይህ ደግሞ መሆን የማይችልበት ምክንያት የለም። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው!

You can reach the author at Gulummaa75_at_gmail.com

Received on Fri Feb 26 2016 - 10:28:50 EST

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved