Zehabesha.com: በጋምቤላ ሁከቱ አይሏል | ፌደራል ፖሊስ ለሰልፍ የወጡትን ዛሬ ጋምቤላ ላይ በጥይት ቆላ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Mon, 25 Apr 2016 00:18:20 +0200

በጋምቤላ ሁከቱ አይሏል | ፌደራል ፖሊስ ለሰልፍ የወጡትን ዛሬ ጋምቤላ ላይ በጥይት ቆላ

ስደተኞቹ ከሃገራችን ይውጡ ሲሉ አደባባይ ትናንት የወጡት ኢትዮጵያውያን በጋምቤላ:: (ፎቶ ከሶሻል ሚዲያ)

ስደተኞቹ ከሃገራችን ይውጡ ሲሉ አደባባይ ትናንት የወጡት ኢትዮጵያውያን በጋምቤላ:: (ፎቶ ከሶሻል ሚዲያ)

(ዘ-ሐበሻ) ጃዊ በሚገኝ የስደተኞች ጣቢያ ላይ በደረሰ የመኪና አደጋ ሁለት መሞታቸውን ተከትሎ; ከደቡብ ሱዳን የመጡ ስደተኞች 15 ኢትዮጵያውያንን (በአብዛኛው የኦሮሞና የአማራ ተወላጅ የሆኑ) በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውን ተከትሎ የጋምቤላ ነዋሪ ትናንት ጀምሮት የነበረውን ሰልፍ ዛሬም ቀጥሎበት ውሏል::

ቁጥራቸው ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሰልፈኞች በአደባባይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ; በስደተኞቹ ሴቶች ሳይቀሩ ብልታቸው ውስጥ እንጨት ተሸንቁሮ መገደላቸውን በማውገዝ ላይ በነበሩበት ወቅት የፌደራል ፖሊስ በአካባቢው ደርሶ ሕዝቡን ለማስቆም ጥይት ተኩሷል:: ከጋምቤላ ለዘ-ሐበሻ የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚያመለክተው ፌደራል ፖሊስ ወደ ኢትዮጵያውያኑ ሰልፈኞች ላይ በተኮሰው ጥይት እስካሁን የታወቁ 5 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል:: ከ15 በላይ ወገኖችም መቁሰላቸው ተሰምቷል::

በጋምቤላ በተለይ የኑዌርም ሆነ የአኝዋክ ብሄረሰብ አባላት ያልሆኑትና በተለይም የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች በስደተኞቹ ተመርጠው መገደላቸው ሕዝቡን ከፍተኛ ቁጣ ውስጥ ከመክተቱም በላይ ለ2ኛ ቀን አደባባይ ወጥቶ ውሏል:: ከስፍራው መረጃዎችን እንዳቀበሉን ወገኖች ገለጻ በአሁኑ ወቅት ጋምቤላ በፌደራል ፖሊስ ከመወረሯም በላይ ሰልፈኞቹ አልፈው ወደ ስደተኞች ጣቢያ እንዳይሄዱ መንገዶች መዘጋጋታቸውን ነው:::

በጋምቤላ ያለው ሁከት በቀጠለበት በዚህ ወቅት መንግስት ከአንድ ሳምንት በፊት በሙርሌ ጎሳ አባላት የተወሰዱትን 125 ህጻናት ጉዳይ መረጃ እስካለመስጠት ደርሷል:: የመንግስት ሚዲያዎች ከአንድ ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ታግተው የተወሰዱት ህፃናትና ሴቶች ያሉበትን ቦታ አውቆ ከቧሸዋል የሚል መረጃዎችን ያስተላለፉ ቢሆንም ከዚያ በኋላ መንግስት ያለው ነገር አለመኖሩና ህፃናቱም ታፍነው የተወሰዱበት ቦታ በረሃብና በበሽታ ከመጋለጣቸው አኳያ መንግስት ምን እያደረገ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው እየተሰነዘሩ ነው::

ከጋምቤላ ተጨማሪ መረጃዎች ከደረሱን ዘ-ሐበሻ አሁንም ለአንባቢዎቿ ከማካፈል አትቆጠብም::

Received on Sun Apr 24 2016 - 18:18:20 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved