Goolgule.com: ለአዲስ አበባ የውሃ ድርቅ “ፈረቃ” መፍትሔ ሆኖ ተበሰረ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 23 Mar 2016 21:44:25 +0100

ለአዲስ አበባ የውሃ ድርቅ “ፈረቃ” መፍትሔ ሆኖ ተበሰረ

በአዲስ አበባ የከርስ ምድር ውሃ ችግር የለም
waterline
 

ራሱን “ልማታዊ” እያለ የሚጠራው ኢህአዴግ በውሃ ድርቅ ሳቢያ በአዲስ አበባ በዝርዝር ባልተገለጹ ቦታዎች ውሃ በፈረቃ ማቅረብ መፍትሔ ሆኖ ተበሰረ። በአገሪቱ በይፋ ያልተገለጸ የውሃ ችግር አለ። አዲስ አበባን በተመለከተ የከርሰ ምድር ውሃ ችግር እንደሌለ ባለሙያዎች ሃሳብ ሲሰጡ ኖረዋል። ኢህአዴግም ቢሆን ከ1997 ምርጫ በኋላ የአዲስ አበባን የውሃ ችግር ለመፍታት የከርሰ ምድር ውሃን እንደሚያጎለብት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነትን ጠቅሶ ቪኦኤ እንደዘገበው የፈረቃው አሠራር የተጀመረው የካቲት 24 ነው። ፈረቃው መፍትሔ ሆኖ የቀረበው የድሬና የለገዳዲ ግድቦች በቂ ውሃ ባለመያዛቸው ሲሆን ፈረቃውም የሚያካትታቸውን ቦታዎች “የተወሰኑ” ከማለት ሌላ ዝርዝር አልቀረበም። በከፊል አዲስ አበባ ተብሎ በደምሳሳው ውሃ በፈረቃ እንደሚታደል ሲገለጽ ፈረቃው ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይም የተሰማ ነገር የለም።

የፈረቃውን ብስራት ተከትሎ በከተማዋ የውሃ ችግር ሥር የሰደደና መፍትሔ ያልተገኘለት ጉዳይ ሆኖ ሳለ ችግሩ ቀደም ሲል የሌለ በማስመሰል ፈረቃ መጀመሩን ማወጅ “ከልማታዊ አስተዳደር” አንጻር አሳፋሪ በመሆኑ ለሦስት ሳምንታት ያህል ይፋ ሳይሆን ቆይቷል። የውሃ ችግር አዲስ አበባን ሰፈር እየለየ ሲጠብሳት መቆየቱን ያወሱት ክፍሎች፣ ችግሩ የዝናብ እጥረት ከመፈጠሩ በፊትም ያለና የነበረ ነው። አሁን አዲስ ጉዳይ ሆኖ ከአየር መዛባትና ከኤልኒኞ ጋር ተዛምዶ ሊነሳ አይገባም ባይ ናቸው።

የአዲስ አበባ አስተዳዳሪ የሆነው ኢህአዴግ በተደጋጋሚ የከተማዋን የውሃ አቅርቦት እናሟላለን በማለት በርካታ ፕሮጀከቶች በሥራ ላይ መሆናቸውን ሲገልጽ እንደነበርና ከመሬት በታች ያለ ውሃ በመጠቀም “የውሃን እጥረት ተረት እናደርጋለን” በማለት ባዶ ተስፋ ሲሰጥ መቆየቱን በክስተቱ የተጠቁት ወገኖች በማስረጃ ያመላክታሉ።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያ እንደሚሉት አዲስ አበባ የከርሰ ምድር ውሃ ችግር የለባትም። አዲስ አበባ እንጦጦ ላይ ሰፋፊ የውሃ ፕሮጀከቶች ቢዘረጋላት በውሃ ምርት ልትጥለቀለቅ እንደምትችል የሚጠቁሙት ከፍሎች “አዲስ አበባ ውሃ ጠማት፣ የውሃ ድርቅ መታት” ብሎ መናገር ለአንድ አገር አስተዳድራለሁ ለሚል ክሽፈት መሆኑን ይጠቁማሉ።

አዲስ አበባ ውሃ በጉቦ ይሰራጭ እንደነበር፣ ድራማውም የሌሎችን መስመር በመዝጋት ጉቦ ለሚከፈሉት በመልቀቅ ገንዘብ ያላቸውን በማንበሻበሽ፣ ገንዘብ ያላቸው ባኟቸው እንዳይደርቅ፣ የሆቴል ትርፋቸው እንዳይስተጓጎል፣ በቀን ሁለቴ ሻወር የሚውስዱ ልማዳቸው እንዳይቀር ወዘተ ድሆችን በውሃ ጥም በማቃጥል ሲከናወን እንደነበር በራሱ ሸንጎ ይፋ መገለጹን በማስታወስ “አዲስ አበባ የከርሰ ምድር ውሃ ችግር ከሌለባት፣ ኢህአዴግም ይህንን ካመነ የውሃ ችግር አዲስ አበባን ለምን ያቃጥላታል?” ሲሉ ይጠይቃሉ። አያይዘውም “ይህ የመልካም አስተዳደር እጦት ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን ግልጽ ክሽፈት ነው። ሕዝብ የሚበላው እና የሚጠጣው ካጣ እንደ አንድ አገር ይህ ውድቅት ነው። የፖሊሲ መኮላሸት ነው። የብቃትና አርቆ በማሳብ የመምራት ድርቅ ነው” በማለት ሃዘናቸውን ይገልፃሉ።

“ይህ ኢህአዴግ የሚባለው ግንባር ቢያንስ በወሳኝና ማህበራዊ በሆኑ አገልግሎቶች ላይ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ቢያሰራ ምን አለበት? ፖለቲካውን ራሱ ህዝብ መፍትሔ እስኪፈልግለት ድረስ ባለሙያዎች አገልግሎት ዘርፎች ላይ እንዲሠማሩ በሩን ቢከፈትላቸው ምን ችግር አለው?” በማለት የኮታና የታማኝነት ሹመት አገሪቱን እያሰመጣት እንደሆነ አሁንም እኚሁ ባለሙያ የተማጽኖ ድምጻቸውን ያሰማሉ። የአዲስ አበባው የጎልጉል ዜና አቀባይ ያነጋገራቸው የውሃ ባለሙያ በዘርፉ በተደጋጋሚ ለመደርደሪያ ሲሳይ የሆነ ጥናት ያቀረቡ ናቸው።

ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኝ ገጠር አንድ ሴትዮ ውኃ በእንስራ ቀድተው ሲሄዱ /ሮይተርስ-REUTERS/

ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኝ ገጠር አንድ ሴትዮ ውኃ በእንስራ ቀድተው ሲሄዱ /ሮይተርስ-REUTERS/VOA

የአዲስ አበባው ችግር ሊደበቅ የማይችል ድረጃ በመድረሱ ፈረቃን ተንተረሶ ይፋ ሆነ እንጂ በየክልሉ ያለው የውሃ ችግር አሳሳቢ ነው። ያልተጣራ ውሃ በመጠጣት ለውሃ ውለድ በሽታ ተጋልጠው ያሉና እድሜ ልካቸውን ጭቃና የማይጠጣ ንጥረ ነገር እየጠጡ የሚኖሩት ወገኖች ችግር የተከደነ ነው። ጎልጉል ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለይም ከሰሜን ምስራቅ አካባቢ የሚደርሱት የህዝብ ምሬቶች ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የፍሎራይድ ማዕድን የሞላበትን ውሃ እየተጋቱ አልጋ ላይ ደርቀው የቀሩ፣ አካላቸው የማይታዘዝ፣ ጥርሳቸው ተፈርፍሮ አልቆ ማላመጥ የማይችሉ፣ አሁንም እነሱም ልጆቻቸውም ይህንኑ ውሃ እየጠጡ የሚኖሩትን ወገኖች ሚዲያውም ገዢያቸውም አያውቋቸውም።

መጠነሰፊና መፍትሔ አልባ በሆኑ ችግሮች ከየአቅጣጫው የተወጠረችውን ኢትዮጵያ ላለፉት 25 ዓመታት በነጻ አውጪ ስም እየገዛ የሚገኘው ኢህአዴግ መሠረታዊ የሕዝብ ፍላጎቶችን ሳያሟላ ልማታዊ፣ ሕዳሴ፣ መልካም አስተዳደር፣ … እያለ እባካችሁ እመኑኝ ቢልም እውነታው ግን የሚያሳየው እንደ መንግሥት ከከሸፈ መቆየቱንና ይህም በራሱ ሰዎች ሳይቀር የሚታመንበት ሃቅ መሆኑን ነው፡፡

Received on Wed Mar 23 2016 - 16:44:26 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved