TGindex.blogspot.de: “ይቅርታ” ወይም “ሰላም”

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Thu, 17 Mar 2016 23:43:18 +0100

“ይቅርታ” ወይም “ሰላም”

Thursday, March 17, 2016
 
ሃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት ያደረጉት ቃለመጠይቅ አነጋጋሪ ነበር። ከኦሮሞ ህዝብ አመፅ ጋር በተያያዘ የሰነበተውን ችግር ሌላ አካል ላይ ማላከክ እንደማይገባ መናገራቸው ከኢህአዴግ ጠባይ አንፃር ያልተለመደ ነበር። በውስጥ ባለ ችግር ምክንያት የህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸው ህዝብና መንግስት ተቃቅረው ጉዳዩ ወደ ግጭት ደረጃ መድረሱን ማመናቸው አንድ እርምጃ ወደፊት ነው። ችግሩ የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን መግለፅ መቻላቸው ይደነቃል። ሃይለማርያም በዚህ ደረጃ ችግሩን አምነውና ተቀብለው ሲያበቁ፤ በመጨረሻ ለተፈጠረው ችግር በጥቅሉ ህዝብን ይቅርታ ጠይቀዋል። ይቅርታ ጥየቃው ካንገት በላይ ነው ወይስ ካንገት በታች ለጊዜው ባናውቅም፤ ይቅርታ መጠየቅ በራሱ ስልጣኔ ነው።
 
እንግዲህ በመቀጠል ወደ ዝርዝር ጉዳይ እንግባ። 
 
ሃይለማርያምይ ቅርታ ሲጠይቁ በመሰረቱ ምን ማለታቸው ነው? ከዚህ በሁዋላ ኢትዮጵያ ላይ በህጉ መሰረት ሰላማዊ ተቃውሞ ማካሄድ ተፈቅዶአል ማለት ነው? ከዚህ በሁዋላ የፌደራል ፖሊስ ሰላማዊ ሰዎችን በየጎዳናው አይገድልም? ባለፉት አራት ወራት እና ከዚያም በፊት በየጎዳናው ለተገደሉት ንፁሃን ዜጎች ወላጆችና ቤተሰብ ካሳ ይሰጣል? ንፁሃን ዜጎችን የገደሉና ያስገደሉ ለፍርድ ይቀርባሉ? የታሰሩት በአስር ሺዎች የሚገመቱ የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ? መሬታቸው ተነጥቆ ለተፈናቀሉ ገበሬዎች ተገቢው ካሳ ተከፍሎ እንዲቋቋሙ ይደረጋል? ይቅርታውን ተከትሎ ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ አንዳችም ያሉት ነገር የለም። በደፈናው ሸውዶ ለማለፍ የተደረገ የለበጣ ይቅርታ ከሆነ ቅዳሴና ዳንኪራን እንደመደባለቅ ይቆጠራል።
 
ከአንድ ሰው ጋር ስለዚሁ ጉዳይ ስንወያይ፣ “ሃይለማርያም ይቅርታ ጠየቀ ለማለት አይቻልም።ይቅርታውን መልሶ አፍርሶታል።” አለኝ። ሌላው ደግሞ፣ “ሃይለማርያም ከዚህ ቀደም ‘አስመራ ሄጄ ከኢሳይያስ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ነኝ’ ሲሉ እንደተናገረው አሁንም የግሉን ይቅርታ ደባልቆ ይሆናል።” አለ። ከዚህ በተጨማሪ “የይቅርታው ቃል በአሜሪካኖች አስገዳጅነት በህወሃት እውቅና የመጣ ነው።” የሚል የውስጥ አዋቂ መረጃም ሰምቻለሁ። ከአስተያየቶች ሁሉ “ይቅርታ” የምትለው ቃል በአሜሪካኖች ተፅእኖ የተነገረች ልትሆን መቻሏ ወደ እውነት የሚጠጋ ይመስለኛል። ሲፃፍ እንደሰነበተው ወያኔ ችግር ውስጥ መገኘቱ አከራካሪ አይደለም። አስረጅ ሊሆን ከሚችለው መካከል፣ “ከኦሮሞ ህዝብ አመፅ ጀርባ የኤርትራ እና የግብፅ ተላላኪዎች አሉ” የሚለውን ክስ ለመተው መገደዳቸው አንዱ ነው። የኦሮሞ ህዝብ አመፅ መነሻ የመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን ማመን እስከዛሬ ጌታቸው ረዳ ሲነግረን የነበረውን ይቃረናል። 
 
ርግጥ ነው፤ ከሃይለማርያም ይቅርታ መጠየቅ ጋር በተያያዘ ከሚሰሙ ጭምጭምታዎች ዋናው የአሜሪካኖች ተፅእኖ ሚዛን የሚደፋ መስሎ መታየቱ ነው። የፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ“ሰላም” የተባለው የማሸማገል ሂደትም የቀጠለ በመሆኑ ምን መልክ ይዞ ይፋ እንደሚሆን በቀጣዩ ጊዜያት የምንሰማው ይሆናል። በአንድ ወቅት CUD የተባለውን ቅንጅት ይመሩ የነበሩ ሰዎች በፕሮፌሰር ኤፍሬም አሸማጋይነት ከእስርቤት ከወጡ በሁዋላ የወያኔ ፍላጎት እንደምንም ተያይዘው ከአገር እንዲወጡለት መንገድ መክፈት ነበር። በርግጥም አብዛኞቹ ባገኙት እድል ሁሉ ተጠቅመው የታገሉላትን አገር ትተው እንደማይመለሱ ሆነው ርቀው ሄደዋል። ይህ ለህወሃት አገዛዝ ጥሩ እድል ነበር። አብዛኞቹየ CUD ሰዎች ከኮበለሉ በሁዋላ ወያኔ እንደ ብርቱካን ሚደቅሳ ያሉትን ነጥሎ ለመምታት አልተቸገረም። 
 
ህወሃት ቅንጅትን አዳክሞ ባጠፋው መንገድ የኦሮሞ አማፅያንን በዚያው ዘዴ ለማኮላሸት ማሰቡ ገና ያልተፈፀመ በሂደት ላይ ያለ ተግባር ነው። እንደሚሰማው የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡን ይቅርታ ጠይቆ እስረኞችን ለመፍታት ለአሜሪካኖቹ ቃል ገብቶ ከሰነበተ እንግዲህ ይቅርታዋ እንደምንም ተነግራለች።  እስረኞችን መፍታትግን ገና አልተፈፀመም። እንደ ውስጥ አዋቂዎች ጥቆማ ከሆነ በእስርቤት ካጎሯቸው በአስር ሺህዎች የሚገመቱ ኦሮሞ እስረኞች መካከል የአመፁ አስተባባሪ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የገመቷቸውን በመለየት ስራ ተጠምደዋል። አመፁን ያስተባብራሉ ብለው የሚገምቷቸውን ለይተው ካበቁ በሁዋላ ወደ ስደት የሚሄዱበትን መንገድ ያመቻቻሉ ተብሎ ይታሰባል። ይህን ማድረግ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ያዳክማል፤ ስርአቱ ትንፋሽ እንዲያገኝም ፋታ ይሰጠዋል ብለው ቢያስቡ ከልምዳቸው አንፃር ስህተት አይሆንም። የነቃው እና የተደራጀው ግለሰብ ከሜዳው ገለል ካለ አመፁ ጠቅልሎ ባይቆም እንኳ ፋታ ሊገኝ ይችላል። በርግጥ እንደ እስክንድር ነጋ፤ እንደ በቀለ ገርባ ለመኮብለል ፈቃደኛ የማይሆኑ ሲገጥሙ ቀመሩ ተገላቢጦሽ ይሆናል። 
 
የኦሮሚያ ወጣቶች ሴራውን ባለመረዳት ለአዲስ ዙር ስደት ከተነሱ ‘በአገሩ የሌለ - የትም የለም።’ እንደሚባለው ለህወሃት ድል ይሆናል።ኮብላዮች ድጋፍ ሰጪ ከመሆን ያለፈ አቅም አይኖራቸውም።የኦሮሞ ህዝብ አሁን ከደረሰበት የተሰሚነት አቅም ላይ እንዲደርስ ያደረጉት በግንባር ቀደምትነት ተጋፍጠው መስዋእትነት የከፈሉት ጥቂት ወጣቶች ናቸው። ድጋፍ ሰጪ ስደተኛ የማድረግ ችሎታው በጣም ውሱን ነው። ሃርቫርድ ከሚገኝ አንድ ተራ ፕሮፌሰር፤ ሃሮማያ የሚገኝ አንድ ተራ የገበሬ ልጅ የተሻለ የማድረግ ችሎታ አለው።ህወሃት ከዳያስፖራ ይልቅ አጠገቡ ያሉትን ተራ ዜጎች ይሰጋል። ስለዚህ የማስቸገር ብቃት ያላቸው ይኮበልሉ ዘንድ ተግቶ ይሰራል። ማሰርና መግደል የህወሃት የመጀመሪያ ምርጫ ሆነው አያውቁም። የኮበለለ ሁሉ የወያኔን የመጀመሪያ ምርጫ እንደተቀበለና እንደተሸወደ ማወቅ አለበት።
 
ባለፈው ሳምንት “የቅዳሜ ማስታወሻ” ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅን በጨረፍታም ቢሆን ነካ አድርጌያቸው ነበር።በላኩልኝ ኢሜይል ስለርሳቸው ያለኝ ግንዛቤ ስህተት መሆኑን ጠቁመውኛል። እርሳቸው እንደገመቱት ሳይሆን ስለ ፕሮፌሰሩ ብዙም ባይሆን ጥቂት አውቃለሁ። የት ከማን እንደተወለዱ፣ የት ምን እንደተማሩ፣ የት ምን እንደሚያስተምሩ አውቃለሁ። ደረጀ ደሬሳ በአጤ ሃይለስላሴ ዘመን በወቅቱ የ31 አመት ጎረምሳ ለነበሩትለአቶ ኤፍሬም ይስሃቅ የፃፈውን መወድስም ኢትዮጵያ ሳለሁአንብቤያለሁ። በተማሪዎች እንቅስቃሴ ዘመን ለአገራቸው ብዙ ቁምነገር የሰሩ ሰው መሆናቸውን ቀደም ብዬም አውቅ ነበር። ሽማግሌው ፕሮፌሰር በጎልማሳነታቸው ዘመን ለደቡብ አፍሪቃ ጥቁሮች መብት መከበር መታገላቸውን በርግጥ አላውቅም ነበር።ዞረም ቀረ የተሰራው መልካም ነገር ሁሉ በቦታው አለ። ታሪክ አይረሳውም፤ ታሪክ ያመሰግናቸዋል።ፕሮፌሰሩ የአባት አገራቸው ታማኝ ልጅ ቢሆኑም፤ መወለድ ቋንቋ ነውና ልክ እንደኔው እሳቸውም የትውልድ አገራቸውን እንደሚወዱ እረዳለሁ። 
 
ፕሮፌሰር ኤፍሬም በደርግ ውድቀት ማግስት የመሸጋገሪያው መንግስት ምስረታ ላይ፣ ታምራት ላይኔን ለማሞገስ፣ “ተአምራት ለአይኔ፣ ተአምር በአይኔ አየሁ” ብለው ቅኔ ሲቀኙ በደማቁ ካጨበጨቡላቸው አንዱ እንደነበርኩ አልክድም። በወቅቱ ሁላችንም ተአምራት በአይናችን ያየን መስሎን ነበር። ታምራትና መለስ የተሸፈነ ጠባያቸው ሳይገለጥ ጥቂት አመታት እንኳ መጓዝ እንደማይችሉ አልገመትንም ነበር። ጃኬትና መኪና ወደ ማማረጥ ይገባሉ ብሎ የጠረጠረ አልነበረም። የሆነው ሆኖ የስካሩ አቧራ ገለል ሲል ፕሮፌሰር ኤፍሬም በአይናቸው ተአምራት ሳይሆን መቅሰፍት ነበር ያዩት። ያም ሆኖ ወዳጅነታቸውን ከወያኔ ጋር ቀጥለዋል።እዚህ ላይ እንግዲህ መነፅራችንን ዝቅ አድርገን፣ “ጤናይስጥልኝ ፕሮፌሰር!” ለማለት እንገደዳለን።
 
ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ የኦሮሞን ህዝብ ከገዢው ግንባር ጋር ለማስታረቅ በሚያደርጉት ሙከራ፣ “ሰላም” የሚለውን ቃል ሲጠቀሙ “የማን ሰላም?” የሚለውንም ጥያቄ ይመልሱት ዘንድ ይጠበቃል።ሰላምን ለማስገኘት ሽምግልና ከመጀመራቸው በፊት “ፀረ ሰላም ማነው? ለሰላም ጠንቅ የሆነው ማነው?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽማግኘት ይገባል። የቀድሞ በጎ ስራ ለዛሬው ስህተት ላጲስ ሆኖ አያገለግልም። “ሰላም ወዳድ” የሚለው ማእረግ “አሻጥረኛ”  ወደሚል ከተለወጠ ለመመለስ ያስቸግራል። የኦሮሞ ህዝብ በአገሩ ላይ የተረጋገጠ ሰላም ለማግኘት መስዋእትነት መክፈል እንዳለበት የተረዳበት ጊዜ ላይ ነው። በርግጥም የአዲሱ ትውልድ መሪ መፈክር አንድ ብቻ ሆኖአል። ይህም፣ “ዛሬ አንድ ነገር ማድረግ አለብን። ወይም ደግሞ መሞት አለብን!” የሚል ነው። እና ማገዙ ካልተቻለ ቢያንስ “እንኳን ለዚህ አበቃችሁ!” ማለት ይገባል።
 
ርግጥ ነው፤ “የሰላም መጥፎ፣  የጦርነት ጥሩ የለውም” የሚለው ነባር አባባል በጥቅሉ ተቀባይነት አለው። ልጇ የሞተባት እናት፤ አባቱ የሞተበት ልጅ ሃዘን ላይ ናቸው። ሃዘናቸውን ለመረዳት እግራችንን እነርሱ ጫማ ውስጥ መጨመር ይገባል። ቢሆንም ግን ለሰላም ሲባል ሰላምን ለማደፍረስ፤ ጦርነትን ለማስወገድ ጦርነት መለኮስ ግዴታ ሆኖ ሊመጣ ይችላል። ሲደፈርስ በርግጥ ብዙ ህይወት ይቀጠፋል። ባይሆን ጥሩ ነበር። ህይወት ሳይከፈል የብዙሃን ሰላም የማይገኝ ከሆነ ግን መደፍረሱ ግድ ይሆናል። ህይወት በሚቀጠፍበት መንገድ ብቻ ማለፍ ግድ መሆኑ ያሳዝናል። በጦርነት ድል ቢገኝም እንኳ ከድሉ ባሻገር አሸናፊውም ልክ እንደ ተሸናፊው እኩል ኪሳራ ይቀበላል። ሰላም አንፃራዊ ነው። በሚዛናዊ መነፅር ስንመለከተው ዚምቧቡዌ ከቀድሞ ሰላሟ ይልቅ የአሁኑ መተራመሷ ይሻላት ይሆናል። በዚህ የዚምቧቤ መተራመስ ውስጥ 300 ሺህ የአገሬው ሰዎች ከዘበኛነትና ከግርድና ስራ ተላቀው ባለመሬት መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም። የኦሮሞ ወጣቶች በዚህ ዘመን የተተወላቸው ስራ በተነጠቀ መሬታቸው ላይ ዘበኝነት መቀጠር ሆኖአል። ከመሬታቸው የተፈናቀሉ የገበሬ ልጆች በዘበኛነት የስራ ዘርፍ አዲሳባን እንደወረሩ፣ በበረንዳ አዳሪነት ከተማዋን እንዳጥለቀለቁ  በቂ መረጃ አለ። እነዚህ ወጣቶች ከጥቂት አመታት በፊት ባለመሬት ነበሩ። ሃብታም መሬት ያርሱ ነበር። ሳሞራ ማሼል ስልጣኑን በያዘባት ሌሊት ያንን ዝነኛ አዋጅ ያወጀው የነፃነትን የተሟላ ትርጉም ለወገኖቹ ለማቅመስ ነበር። ነፃነት ሲባል የከበርቴ ሰዎች ዘበኛ ሆነህ መለፍለፍ መቻል ማለት አይደለም። ነፃነት ከመሬት ባለቤትነት ይጀምራል። እና ሞዛምቢካውያን ከነሙሉ ችግራቸው ዛሬም ቢሆን ሳሞራን በበጎ ያስታውሱታል።  
 
የኦሮሞ ህዝብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስርአቱ የጫነበትን የሰቆቃ ህይወት እየተቃወመ ረጅም ተጉዟል። ሸክሙ ሲበዛበት ግን ቀንበሩን ወረወረና አታላዩን ሰላምና ፀጥታ ክፉኛ አደፈረሰው። የህልውና ጉዳይ ሆነበት። አይኑ እያየ የማያውቃቸው ሰዎች መጥተው የአያቱን መሬት ሲሸጡ ሲመለከት የሰላም ትርጉሙ ጠፋበት። መሞትን መረጠ። እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰን ሰው “ለሰላም ሲባል”፤ “ለአንድነት ሲባል” ብለህ ልታግባባው አትችልም። አይሰማህም። በአንድ ወቅት የOPDO ምክትል ሊቀመንበር እንደነበረው እንደ ኢብራሂም መልካ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “ለኦሮሞ ያልሆነች ኢትዮጵያ አስር ቦታ ትበጣጠስ!!” ሊልህ ይችላል። በመሆኑም ፕሮፌሰር ኤፍሬም ለማን ጥቅም እየሰሩ እንዳሉ ማወቅ አለባቸው። ለኢትዮጵያ አንድነት? ለተጨቆኑ ህዝቦች ሰላም? ወይስ ለአንድ ቡድን ስልጣን? ምላሹ ለህሊናቸው ይሁን።
 
የጃዋር መሃመድን መረጃ ከያዝን ሌላው ይቆይልንና ባለፉት አራት ወራት በኦሮሚያ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 500 አሻቅቦአል። ይህ ብቻውን እንኳ ለወያኔ ትልቅ እዳ ነው። ክፍያው ሊቸግር ይችላል። የህይወት እዳ ወለዱ ውድ ነው። ሃይለማርያም በቅርቡ ሴት ልጃቸውን በሞቀ ሰርግ ድረዋል። ሟቾቹ ወጣቶች በተመሳሳይ ለወግ ለማእረግ እንዲበቁ ወላጆቻቸው ይመኙ ነበር። ልጆቻቸውን ያጡ፣ አባታቸውን የተነጠቁ ወገኖች ሃዘኑን አይችሉትም። ሃይለማርያም ይቅርታ የጠየቁት በራሳቸው ተነሳሽነት ከሆነ ከዚያም በላይ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ርግጥ ነው፤ “የኦሮሚያ አመፅ” የሚለው የጨዋታ ካርድ ላለፉት አራት ወራት ከፖለቲካ ሜዳው ላይ ሊወርድ አልቻለም። ከቀዳሚ ዜናነቱ ሊገፈተር አልቻለም።ሰበር ዜና ከመሆን ሊታቀብ አልቻለም።ሃይለማርያም የበታች አለቆቻቸውን ስነልቦና መረዳት ይጠበቅባቸዋል። አባይ ፀሃዬ እና ስብሃት ነጋ “ጥቂት ታገስ! ከዚያም ጊዜ ጠብቀህ የጨዋታውን ካርድ ቀይረው” የሚለውን የሰርቫንቴስ አባባል ደጋግመውም ይጠቀሙበታል። የ“ይቅርታ” እና የ“ሰላም” ወጎች የትእግስት ምእራፍ ሲሆኑ፤ ከረምረም ብለው የጨዋታውን ካርድ ለመቀየር መሸጋገሪያ ይሆናሉ። ያንጊዜ ጊሎቲን አንገት ቆረጣውን እንዳዲስ ይጀምራል። 
 
በመጨረሻ አንድ ነጥብ ላይ ላስምር። የኦሮሞ ህዝብ እየከፈለ ያለው የህይወት መስዋእትነት ኪሳራ አይደለም። ግብና አላማ አለው። ለመጪው ትውልድ እየተከፈለ ያለ የክብር ዋጋ ነው። እና የኦሮሞ ህዝብ ጨክኖ እንደጀመረ ከመግፋት በቀር አማራጭ የለውም። ወደሁዋላ ማየት እንደገና መቶ አመታት ሊያስተኛ ይችላል። መስዋእትነቱን አያስቀረውም። ከመሬት መፈናቀሉን፣ ስደቱን አያስቀረውም። የኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ህዝብ እንደመሆኑ ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን አስተባብሮ፣ አቅፎ ወደ ተሻለው ዘመን የመጓዝ ብቃቱና ችሎታው አለው። ያለ ኦሮሞ ህዝብ ኢትዮጵያ ምትባል አገር የለችም። እና የኦሮሞ ህዝብ ራሱን ነፃ ከማውጣት ባሻገር ከባድ ሃላፊነት አለበት። የተረጋገጠውን ሰላም ለማግኘትና በረጅሙ ለማረፍ ጨለማማውን ጫካ በድፍረት ማለፍ ይገባዋል። ይቻለዋልም። አሳምሮ ይቻለዋል። ታግለው ነፃ የወጡ የአለም ህዝቦች ታሪክ የሚነግረን ይህንኑ ነው።
 
የቅዳሜማስታወሻ   Gadaa Ghebreab  ttgebreab_at_gmail.com  www.tgindex.blogspot.com   March 17  2016
 
 
Received on Thu Mar 17 2016 - 18:43:19 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved