Goolgule.com: ብሶት የወለደው የኦሮሚያ አመጽ ተቆንጥሮ አስመራ ላይ ተላከከ!

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 1 Mar 2016 13:51:33 +0100

“ለህወሃት ብቻ የትጥቅ ትግልን ህጋዊ ያደረገው ማን ነው?”

getachew -reda-ethiopia
march 01, 2016 06:39 amt
 

በኦሮሚያ የተነሳውን ህዝባዊ እምቢተኛነትና ዓመጽ ተከትሎ ስለጠፋው የሰው ህይወት እርግጠኛ አሃዝ የሚጠቅስ አልተገኘም። ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና የአገር ውስጥ ቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደሚሉት የህወሃት አንጋቾች ከ200 በላይ ንጹሃንን ገድለዋል። በነጻ አውጪ ስም አገሪቱን እየመራ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር – ህወሃት፣ አመጹን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ ቆይቶ በስተመጨረሻ ችግሩን ቆንጥሮ አስመራ ልኮታል። ወታደርና ከባድ መሣሪያም ወደ ድንበር አስጠግቷል። መፍትሔው ጭፍን ብሔረተኝነት ሳይሆን ሁሉንም በሰብዓዊ ፍጡርነት ማየት ነው የሚሉ አካላት “ጆሮ ያለው ይስማ፣ ልቡና ያለው ያስተውል” እያሉ ነው፤ ርምጃቸውንም ከጊዜ ጋር አዋዝተዋል። ህወሃት የትጥቅ ትግልን የራሱ “ንግድ ምልክት” አድርጎ መውሰዱ የማይዋጥላቸው “ለህወሃት ብቻ የትጥቅ ትግልን ህጋዊ ያደረገው ማን ነው?” በማለት ይጠይቃሉ፡፡

“ታዛዥ” በሚል ስያሜ የሚጠሩትና ብዙም ከበሬታ የሌላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ “የማያዳግም ርምጃ እንወስዳለን” ባሉ ማግስት የተምታታ መግለጫ በመስጠት ዝነኛ እየሆኑ የመጡት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ የምዕራብ አርሲውን ችግር አስመራ ላይ ለጥፈውታል። ሠራዊት አዝምቶ ንጹሃንን እየጨፈጨፈ ያለው ህወሃት፣ በሃይለማርያም ደሳለኝ አንደበት “የማያዳግም ርምጃ እንወስዳለን” ማለቱን ተከትሎ “እየገደሉ ነው፣ እያሰሩ ነው፣ እየገረፉ ነው፣ እያቆሰሉ ነው፣ የማያዳግም ሲባል ነፍሰጡር ከመግደል የዘለለ ምን አይነት ርምጃ ሊሆን ነው?” ሲሉ አስተያየት የሰጡት የአርሲ ኮፈሌ ነዋሪ ናቸው።

ሌላ ገለለተኛ አስተያየት ሰጪ “እኔ በግሌ ስርዓቱን የማላምንበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ፣ ብዙ ሰዎች ራሳቸው ኢህአዴጎቹን ጨምሮ ከነባለሥልጣኖቻቸው ልባቸው ሸፍቷል። አገር የሚመራ ድርጅት ካልታመነ አደጋው የከፋ ይሆናል” ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። ማሳያ በማቅረብ ሲቀጥሉም ሙሽሮች ቀስቃሽ ዘፈን አሰሙ በማለት ተኩስ በመክፈት ሠርገኞችን አቆሰሉ፤ ሙሽሮቹ ሸሽተው ጫካ ገብተው ከሁለት ቀን በኋላ ተገኙ፤ ህዝብ ተቆጣና ጠመንጃ አንግተው የሚገሉትን ገደለ፤ ይህን እውነት ለምናውቅ “ጉዳዩ ከሰላማዊ ተቃውሞ ያፈነገጠ ሽብር ነው ተብሎ ሲነገረን ምን እንበል? ከዚህ በላይ እምነትን የሚሸረሽር ምን አለ?” በማለት ይጠይቃሉ፡፡

ኢህአዴግ ከበረሃ ወደ ቤተመንግስት ሲዛወር የእድሜ ልክ ጠላቱ አድርጎ የሚያሰቃየውን አማርኛ ተናጋሪ ህዝብ ማስፈጀት የጀመረው አርሲ እንደሆነ የሚያስታውሱ ከፍሎች አሁን ህወሃት “ምዕራብ አርሲ ላይ የታየው የተለየ ሽብርና ስልጣንን ኢ-ህግመንግስታዊ በሆነ መልኩ ለመጨበጥ ያለመነው፣ በጉዳዩ ላይ የአስመራው መንግስት እጅ እንዳለበት ማስረጃ አለ” በሚል ለውጭ ሚዲያዎች መግልጹን በርካቶች አይቀበሉትም።

የቬንዝዊውላ አምባሳደር የሆኑት ራፋኤል ዳርዮ ራሚሪዝ ካሬኖ የማዕቀቡን ኮሜቴ ስራዎች አስመልክተው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ሲያስረዱ፣ “ቡድኑ የኤርትራ መንግስት አልሸባብን እንደሚደግፍ የሚያሳይ ማስረጃ አላገኘም” ባሉ ማግስት ህወሃት ይህንን መሰል መረጃ ይፋ ማድረጉ መረጃውን የተዛባ እንደሚያደርገው እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ።

ከዚሁ ጋር በተያያዝ ይሁን በሌላ ህወሃት በሰሜን ጎንደር ሱዳን ድንበር ኤርትራ ላይ ያነጣጠረ ሰራዊትና ከባድ መሳሪያ ከወትሮ በተለየ መልኩ ማሰለፉ ተሰምቷል። ኢሣትና አንዳንድ ድረገጾች ዜናውን ይፋ ከማድረጋቸው ውጪ ከህወሃት በኩል በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ኢሳያስ አፈወርቅን በማስወገድ ራሱ ያደራጀውን መንግስት ኤርትራ ላይ ለመትከል ደፋ ቀና ማለት ከጀመረ ዓመታትን ያስቆጠረው ህወሃት፣ ይሳካ አይሳካ ባይታወቅም በተመሳሳይ መልኩ ህወሃትን ለማሰወገድ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ሻዕቢያ ማገዙ እንደወንጀል ይቆጠርበታል። ተቃዋሚዎችን ማደራጀት የሽግግር መንግሥት መመሥረት ለህወሃት ህጋዊ ሲሆን፣ ለሻዕቢያ ወንጀል ተደርጎ ተወስዷል።

ህወሃት በተገንጣይ ስም የሚጠራበትን “ታላቅ የመሆን” ህልሙን እውን ለማድርግ ኤርትራ ላይ የራሱን ስሪት መንግስት ለማቋቋም ሌት ተቀን ሲሰራ፣ ሻዕቢያ ብዙም ሲከሰው አይሰማም። በኢትዮጵያ የውስጥ ችግር ሲባባስ ሻዕቢያን መወንጀል፣ ማስፈራራት፣ ማሳጣት፣ ተቃዋሚዎችን “ተላላኪ” በማለት ለማሳነስና ክብረቢስ አድርጎ ለመሳል መሞከር፣ ወዘተ የተለመደ የህወሃት ተግባር መሆኑ በተደጋጋሚ የሚሰማ ጉዳይ ነው።

ለዚህም ይመስላል የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አዳባ ባለፈው ዓርብ ለቪኦኤ ሲናገሩ ይህንን ጉዳይ ያሰመሩበት። የሳዳም ሁሴን የማስታወቂያ ሚኒስትር የአሜሪካ ወራሪ ጦር ባግዳድን ሲቆጣጠር እሳቸው የመድፍ ድምጽ በሚሰማበት ስልካቸው “ችግር የለም” ዓይነት መልስ ይሰጡ ነበር። በሰሞኑ መግለጫቸው ከእኚሁ ሚኒስትር ጋር የተመሳሰሉት አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ ለሰነዘሩት ክስ መልስ የሰጡት አቶ ቶሌራ “ስልጣን ላይ በመቆየታቸው የነበሩበትን ሁኔታ የዘነጉ ይመስላሉ። ለህወሃት የትጥቅ ትግልን ህጋዊ አድርጎ ኦነግን የሚከለክል ህግ የለም” ብለዋል።

ተመሳሳይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች በምዕራባውያን ዕርዳታ፣ ድጎማና በኢትዮጵያ ላይ ባላቸው ጥላቻ እየተደገፈ “የትጥቅ ትግል አካሂጄ ድል አደረኩ” የሚለው ህወሃት የትጥቅ ትግልን የራሱ ብቸኛ “የንግድ ምልክት” አድርጎ መውሰዱ የማይሠራና አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አኳያ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ እነዚሁ ወገኖች እንዲያውም ይህ የህወሃት አስተሳሰብ ነጻነትን የመጎናጸፊያው ብቸኛ መንገድ የትጥቅ ትግል ነው ብለው እንዲያምኑ በርካታዎችን እያደረጋቸው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

ከፋሽስት ጣሊያን ባልተናነሰ ሁኔታ ህጻናትን፣ ነፍሰጡርን፣ አዋቂዎችን፣ አረጋውያንን፣ የሚጨፈጭፍው ወያኔ ወንጀሉን ለመሸፋፈን የሚያደረገው መፍጨርጨር መሆኑንን በመግለጽ የቀረበባቸውን ክስ ያጣጣሉት የአርበኞች ግንቦት 7 የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ነዓምን ዘለቀ “ጌታቸው ረዳናመሰሎቹ ለፍርድ የሚቀርቡበት ቀን ሩቅ አይሆንም” ሲሉ ህወሃትን ራሱ “መንግሥታዊ አሸባሪ ነው” ሲሉ ጠርተውታል።

ኦፌዴንም ከፊል አባሎቹ አሸባሪ ተብለው መከሰሳቸውን አስመልከቶ ድርጅቱ ከሽብር ጉዳዮች ጋር ግንኙነት እንደሌለው፣ አምባገነንነትን እንደሚዋጋ፣ ሕዝብ ለሚያቀርበው ጥያቄ አግባብነት ያለው መልስ መሰጠት እንዳለበትና ብቸኛውም አማራጭ ሕዝብን ማክበር መሆኑንን በመግለጽየጌታቸው ረዳን ስሞታ አጣጥለውታል።

በአገር ውስጥ የተከሰተውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ወደ አስመራ መውሰድ እና ከኤርትራ ጋር ማዛመድ በኦሮሚያ ላይ “የማያዳግም ርምጃ እንወስዳለን” የሚለውን የህወሃት አካሄድ “ሕጋዊ” ሽፋን ለመስጠት የታሰበ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ታዛቢ ለጎልጉል በሰጡት አስተያየት መሠረት “ኤርትራ አሸባሪ ከተባለች በኋላ የኦሮሚያ ተቃውሞን ከኤርትራ ጋር ማዛመድ በቀጣይ ለመውሰድ ለታሰበው እርምጃ “አሸባሪነትን ለመከላከል የተወሰደ” የሚል የአገር ውስጥና ዓለምአቀፋዊ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት ያስችላል፤ አሜሪካ አፍጋኒስታንን አሸባሪ ካለች በኋላ ድንበር አልፋ፤ ባሕር አቋርጣ አፍጋኒስታንን ለመደብደብ ሕጋዊ ሽፋን እንዳገኘች ሁሉ ይኼኛውም የህወሃት አካሄድ ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት አለው” ብለዋል፡፡ (ፎቶ: ተስፋዜና)

Received on Tue Mar 01 2016 - 07:51:34 EST

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved