Ethsat.com: 1. የኢህአዴግ ከፍተኛ ካድሬዎች በድርጅታቸው ግራ ተጋብተዋል 2. በሱዳን በኩል ወደ ውጭ የሚወጡ ዜጎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 5 May 2015 00:37:05 +0200
May 4, 2015

ሚያዝያ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያንን ለመዘከር የወጣው ህዝብ ተቃውሞውን ወደ ኢህአዴግ መንግስት ካዞረ በሁዋላ፣ ገዢው ፓርቲ ተቃውሞውን ያስነሳው በአገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የሚታገለው ሰማያዊ ፓርቲ ነው በማለት የከፈተው ሰፊና አሰልቺ ፕሮፖጋንዳ የህዝቡን አመለካከት ሊቀይር አለመቻሉ ከፍተኛ ካድሬዎችን ስጋት ላይ ጥሎአቸዋል፡፡

በመስቀል አደባባይ የታየውን ህዝባዊ ቁጣ  ሰማያዊ ፓርቲ የቀሰቀሰው የመንደር ሁከት ለማስመሰል በስሩ በሚገኙ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ፕሮፖጋንዳ የሰራ ቢሆንም ፣ ፕሮፓጋንዳው ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን የራሱን አባሎች ማሳመን አለመቻሉ ከፍተኛ ካድሬዎችን ድንጋጤ ላይ ጥሎአቸዋል።

በአዲስአበባ አስተዳደር በተለያዩ የመንግስት ቢሮዎች  ይህንኑ የሕዝብ ተቃውሞ በማስመልከት ሰማያዊ ፓርቲ ያቀነባበረው መሆኑን በመግለጽ ሁኔታውን ለማውገዝ ታስቦ ሰሞኑን ተከታታይ ስብሰባዎች የተካሄዱ ቢሆንም አጥጋቢ ውጤት ሊገኝባቸው አልቻለም፡፡

በተለይ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ጭምር ፍረጃው አሳማኝ አለመሆኑን በመጥቀስ ሕዝቡ በተለይ በመልካም አስተዳደርና በኑሮ ውድነት ችግሮች ውስጥ ሆኖ መቃወሙ የሚጠበቅ እንደነበር፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ይልቅ ወደውስጣችን በመመልከት ችግሩን ካልቀረፍን ከዚህም የባሰ ችግር ሊገጥመን ይችላል በሚል የተንጸባረቁ ደፈር ያሉ አስተያየቶች ያልተጠበቁ በመሆናቸው የመድረክ መሪ ካድሬዎችን ጭምር አስደንግጦአል፡፡

አንድ የሰብሰባው ተካፋይ “በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ አንድ በወር 3 ሺህ ብር የሚያገኝ መካከለኛ ገቢ ያለው የሚባል ደመወዝተኛ ቤት ኪራይ፣ የትራንስፖርት፣ የቤተሰብ ቀለብና የመሳሰሉ ወጪዎችን መሸፈን ጨርሶ አይችልም፡፡ አነስተኛ ወርሃዊ ገቢ ያለው ሰፊ የህብረተሰብ ክፍል ከሞቱት በላይ ፣ከቆሙት በታች ሆኖ የሰቆቃ ኑሮ እየገፋ በመሆኑ ተቃውሞ ሲያንሰው ነው” ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልጸውለታል፡፡ በአንጻሩ ግን ቤት መኪናና የተሻለ ገቢ ያላቸው ሹማምንት ከደሃውን ጉሮሮ እየነጠቁ በሙስና የሚከብሩበት ስርኣት መፈጠሩ ግልጽ ሆኖአል ሲሉ አክለዋል።

ኢህአዴግ በተለያዩ መዋቅሮቹ ሰማያዊ ፓርቲ ከግንቦት 7 ጋር በማበር ሁከት በመቀስቀስ ላይ ነው በሚል የተጠናከረ ፕሮፖጋንዳ ከሰራ በሃላ ያለችግር ፓርቲውን ከምርጫ ለማስወጣትና የተወሰኑ አመራሮችንም ለማሰር አቅዶ የነበረ መሆኑን የጠቀሰው ለጉዳዩ ቅርበት

ያለው ምንጫችን ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይህ ዕቅዱ እንዳሰበው በቀላሉ የሚሳካለት ባለመሆኑ ከፍተኛ ካድሬዎቹ በድንጋጤና በግራ መጋባት ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል ብሎአል።

በሌላ በኩል በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን ለመዘከር የሻማ ማብራትና የጸሎት ስነስርአቶች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው። በደቡብ ኮሪያ ሴኡል ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያኞች ለሟቾች ሀዘናቸውን ገልጸው፣ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው በስልጣን ላይ ያለው ሃይል ነው ብለዋል። ኢትዮጵያኑ በፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ እድል በማጣታቸው መሰደዳቸውን የገለጹት ኢትዮጵያኑ ፣ ከዚህ ችግር የምንላቀቀው ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርአት ሲመሰረት ብቻ ነው ብለዋል።

በሻርሎቴ ኖርዝ ካሮላይና  የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንም በተመሳሳይ ሻማ ማብራትና ጸሎት ስነስርአት በማድረግ የተገደሉትን ኢትዮጵያውያንን አስበዋል። ኮንግረስ ማን ሮበርት ፒተንገር እና የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች በስፍራው ተገኝተው መልእከቶችን አስተላልፈዋል።

***************************************************************

በሱዳን በኩል ወደ ውጭ የሚወጡ ዜጎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል
 
May 1, 2015

ሚያዝያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በዚህ ሳምንት ብቻ 9 ሺ 405 ወጣቶች ድንበር አቋርጠው ወደ ሱዳን ሲጓዙ በድንበር ጠባቂ ፖሊሶች ተይዘዋል።

ፋሲል የኔአለም ዝርዝሩን ያቀርበዋልበሰሜን ጎንደር ዞን ቆላማ ወረዳዎች በተደረጉ 2 የዳሰሳ ጥናቶች በቀን  ከ150-250  በዓመት ደግሞ ከ 54,000 እስከ 90,00 ኢትዮጵያውያን   ወደ  ሱዳን ይሻገራሉ፡፡ ጥናቱ በመላው አማራ ወይም በመላው አገሪቱ ያለውን የስደት ቁጥር አይዳስስም።

በዚህ ሳምንት ብቻ ወደ ሱዳን   ለመሻገር የሞከሩ   9 ሺ 405  ግለሰቦች በጸጥታ ሃይሎች ሲያዙ፣ የጃን አሞራ ፖሊስ ጽ/ቤት ለኢሳት በላከው  መረጃ መሰረት በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁሉም ሴቶች ናቸው።  ከእነዚህ  ሴት ስደተኞች ውስጥ 66 በመቶው ከ18  እስከ 24 እድሜ ያላቸው ሲሆን፣ 32 በመቶው ደግሞ ከ14 አመት በታች ናቸው።  ወደ ሱዳን በመፍለስ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የአርማጭሆ፣ በየዳ፣ ጃናሞራና ወገራ ወረዳዎች ሲሆን፣ በአካባቢው ያለው ድህነት ከሁሉም አካባቢዎች የከፋ ነው፡፡

ስደትን ከድህነት ማምለጫ አድርገው የወሰዱት በርካታ  ህፃናትና  ሴቶች  በረሃ ላይ ሞተው  የሚቀሩ  ሲሆን ፣ ወደ ስደት በመሄድ ላይ እያሉ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ መተማ  ዮሃንስ  ጤና  ጣቢያ  የመጡ 26ት ሴቶች በተቅማጥ፣ በመኪና አደጋ፣ በድብደባ ፣ራስን በማጥፋትና በሌሎችም ምክንያቶች ህይወታቸው አልፎአል። አለማቀፍ ስደተኞች ድርጅት /IOM/ በ2013 ባወጣው ጥናት ሳውዲ አረቢያ ፣ የመን፣የተባበሩት አረብ ኢምሬትና ወደ ሌሎች  አገሮች በአመት ከ400ሺ-500  ሺ የሚሆኑ ዜጎች ከአገር ይወጣሉ።

በመተማ መስመር በቀን በአማካኝ ከ150-250 የሚሆኑ ሰዎች ወደ ሱዳን ፣ በአፋር መስመር ደግሞ በቀን በአማካኝ እስከ 80 የሚደርሱ ሰዎች ወደ ጅቡቲ ይሰደዳሉ።

ከአማራ ክልል ከሰሜን ወሎ እና የሰሜን ጎንደር ወረዳዎች፣ ከኦሮሚያ ክልል ደግሞ ከጅማ እና አርሲ አካባቢ የሚመለመሉ እድሜያቸው ከ18 ዓመት የማይበልጡ ሕፃናት ሴቶች በመተማ ሱዳን በኩል ይሻገራሉ። አብዛኞቹ ስደተኞች ሱዳን ከደረሱ በኋላ ሴቶች ለቤት ሠራተኝነት የሚቀጠሩ ሲሆን ወንዶች ደግሞ በእርሻ ቦታዎችና በኮንስትራክሽን ድርጅቶች በቀን ሠራተኝነት እንደሚሰማሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

በአፋር ከልል ጅቡቲ መስመር የሚሰደዱት ደግሞ  በአብዛኛው ከአማራ እና ከትግራይ ክልል የሚመጡ ሲሆን በተወሰነ መልኩም የኦሮሚያና የደቡብ ክልል ነዋሪዎች ይገኙበታል፡፡ በዚህ መስመር ከሚጓዙት ውስጥ አብዛኞቹ ከሚሴ፣ ባቲ፣ ወረኢሉ፣ ወረባቦ፣ ቢስቲማ፣ ቦከክሳ፣ ኮምቦልቻ፣ ጊራና፣ ዋድላናደላንታ፣ ወልድያ እና መርሣ ናቸው፡፡ አልፎ አልፎም ከሰሜን ሸዋ አካባቢዎች መነሻ በማድረግ በየቀኑ በቡድን በመሆን ከ10-80 የሚሆኑ ሰዎች በአንድ ላይ ተሰባስበው የአፋርን ክልል በማቋረጥ ከሀገር የሚወጡ ሲሆን በብዛት የሚሄዱባቸው መዳረሻ ሀገራትም ጅቡቲ፣ ሳውዲዓረቢያ፣ የመንና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ናቸው፡፡

በኬኒያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪቃ የሚጋዙት ደግሞ በአብዛኛው ከደቡብ በተለይም ከከንባታና ከሀድያ አካባቢዎች የሚነሱ ዜጐች ናቸው።

በእነዚህ መስመሮች ከሚወጡት ኢትዮጵያውያን መካከል ቁጥራቸው ቀላል የማይባል፣ በሊቢያና ሱዳን በረሃዎች ፣ በቀይ ባህርና በሜዲትራኒያን ባህሮች ህይወታቸው ያልፋል። ታሳክቶላቸው ወደ ተለያዩ አገራት የደረሱት ደግሞ በቅርቡ በሳውድ አረቢያ፣ የመን፣ ሊቢያና ደቡብ አፍሪካ እንደተመለከትነው አስከፊ የሆኑ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸዋል።

መንግስት በአሁኑ ጊዜ የስደቱ ምንጭ ህገወጥ ደላሎች ናቸው ቢልም ብዙዎቹ ግን አይስማሙም። በአገሪቱ ውስጥ የተንሰራፋው ስር የሰደደ ድህነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ጭቆናውና ሙስና ዜጎችን ለስደት እየዳረጉ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።

በገጠር የአገሪቱ ክፍል ያለው የእርሻ መሬት ጥበት ብዙ አርሶአደሮች መኖሪያቸውን እየተዉ ወደ ከተማና ወደ ውጭ እንዲሰደዱ እያደረጋቸው ነው። በከተማ ደግሞ የስራ አጡ ቁጥር ከመቼም ጊዜ በላይ ጨምሯል። በቅርቡ አይ ሲስ የተባለው አክራሪ እስላማዊ ታጣቂ ሃይል እንዲሁም  በአገራቸው ያሉ ስደተኞች እንዲወጡ የሚጠይቁ ደቡብ አፍሪካውያን በኢትዮጵያ ስደተኞች ላይ የወሰዱት አስከፊ እርምጃ የአገሪቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ በሆነበት ወቅት፣ አሁንም ሞትን ፊት ለፊታቸው  እያዩ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሲጨምር እንጅ ሲቀንስ አለመታየቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

ኢትዮጵያውያን  በአገሪቱ ውስጥ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ አፋጠኝ መፍትሄ ካላበጁ ፣ አገሪቱ በቀላሉ ወደ ማትመለስበት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ትወድቃለች በማለት እያሳሰቡ ነው።

Received on Mon May 04 2015 - 18:37:06 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved