Ethsat.com: በሃረር የቀን ሰራተኞች ታፈሱ፣ እድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱትም ወደ ማሰልጠኛ ካምፖች ተወሰዱ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Mon, 9 Mar 2015 21:00:39 +0100

በሃረር የቀን ሰራተኞች ታፈሱ፣ እድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱትም ወደ ማሰልጠኛ ካምፖች ተወሰዱ

March 9, 2015

የካቲት ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሃረር ከተማ ካለፈው ሁለት ሳምንት ጀምሮ እንዳዲስ በተጀመረው አፈሳ በርካታ በቀን ስራ የሚተዳዳሩ ነዋሪዎች ታፍሰው ወደ አልታወቀ ስፍራ የተወሰዱ ሲሆን፣ አንዳንድ ወገኖች ግን ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ተወስደዋል ብሎዋል።  እሁድ እለት ደግሞ  በርካታ  አዲስ ምልምል ታዳጊዎች ደግሞ ለወታደራዊ ስልጠና ወደ ብር ሸለቆ ተወስደዋል። እድሜያቸው ከ12 እስከ 13 አመት የሚደርሱ ወጣቶችም ወደ ማሰልጠኛ የተወሰዱ ሲሆን፣ ወላጆች የትውልድ ዘመን ማስረጃ ሰርቲቪኬት ይዘው ቢሄዱም፣ መልስ  ሊያገኙ አልቻሉም። ሸንኮር፣ ካናዳ አምባና 17 በሚባሉት አካባቢዎች እናቶች በልጆቻቸው  መሄድ  ሲያልቀሱ  ነበር።

ከጎዳና ላይ እየታፈሱ የተወሰዱት ነዋሪዎች ያለፍላጎታቸው ቢወሰዱም ፣ ሌሎች ግን በወጣው ማስታወቂያ መሰረት መመዝገባቸውን ወኪላችን ገልጿል። ይሁን እንጅ በፈቃደኝነት ተመዘገቡ የተባሉት ብዙዎቹ  ታዳጊዎችና እድሜያቸው ከ12 -13 እንደሚሆናቸው ገልጾ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስቀረት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ በመቅረቱ ለሃዘን ተዳርገዋል። ወጣቶቹ በመከላከያ ውስጥ የተሻለ ትምህርትና የውጭ እድል እንደሚያገኙ ተነግሮአቸው መመዝገባቸውም ወኪላችን አክሎ ገልጿል።

የሃረሪ ክልል ለመከላከያ ሰራዊት የሰው ሃይል አላዋጣም በሚል ከፍተኛ ግምገማ ቀርቦበት ነበር። ያንን ኮታውን ለማሟላት በሚመስል መልኩ እድሜና ፍላጎትን ግምት ውስጥ ሳያስገባ ወጣቶችን ወደ ማሰልጠኛ እንደላከ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘገባውን አጠቃሏል።

ኢሳት በአፋር ክልል በተመሳሳይ መንገድ ወጣቶች ታፍሰው መወሰዳቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

********************************************************************************

በጋምቤላ የድንበር ከተሞች ዜጎች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች እየተገደሉ ነው

March 9, 2015

የካቲት ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለደቡብ ሱዳን አዋሳኝ በሆኑ የጋምቤላ አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን በየጊዜው እንደሚገደሉና የጸጥታው ሁኔታ እየተበላሸ መሆኑን በተለያዩ የመንግስትና የግል ስራዎች ላይ የተሰማሩ ዜጎች ገልጸዋል።

መታሃር፣ ላሬ፣ ኢታንግ እንዲሁም ፑጊዶ በሚባሉ አካባቢዎች ማንነታቸው በውል የማይታወቁ ታጣቂዎች አብዛኛውን ጊዜ በግል ኩባንያዎች ተቀጥረው በሚሰሩ ዜጎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ነው። እነዚህ ታጣቂ ሃይሎች የሚወስዱትን እርምጃ ተከትሎ የፌደራል ፖሊስና ልዩ ሃይል አባላትም በንጹሃን ዜጎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስዱ ነዋሪዎች ይገልጻሉ። የካቲት 13 ቀን ማቲያስ ዘነበ የተባለው የታያም ኢንጂነሪንግ ኩባንያ አማካሪ ተገድሎ አስከሬኑ ወደ ደብረዘይት ተሸኝቷል። በሌሎች አካባቢዎችም እንዲሁ በየጊዜው ሰራተኞች እየተገደሉ አስከሬናቸው ወደ መሃል አገር እንደሚሸኝ ይናገራሉ።

በአካባቢው የሚታየውን የመሬት መቀራመት በመቃወም የአካባቢው ተወላጆች በተቀጣሪ ሰራተኞች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ አድርጓቸዋል የሚሉት ነዋሪዎች፣ መንግስት በቂ የሆነ እልባት ማስገኘት እንዳልቻለም ያክላሉ።

በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚናገሩት በጋምቤላ ከውጭ አገር ባለሃብቶች ቀጥሎ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን የያዙት የህወሃት ባለስልጣናት ናቸው። በተለይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍንና የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪ አባይ ጸሃየ ዘመዶች እጅግ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን እንደያዙ ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ። ወ/ሮ አዜብ በተር ፍላይ አግሮ እንዱስትሪ (butterfly Agro Industry) በተበለ ኩባንያቸው ሰፊ መሬት ይዘው ቢቀመጡም፣ ቦታውን እስካሁን አላለሙትም። እንደነዚህ ሰዎች አገላለጽ፣ የባለስልጣኖቹ ዘመዶች ሰፋፊ ቦታዎችን ከክልሉ ባለስልጣናት ይረከቡና ከባንክ ብድር ይወስዱበታል፣ በተበደሩት ብድር ግን የእርሻ ቦታውን ከማልማት ይልቅ፣  ሌሎች ስራዎችን ይሰሩበታል።

የጋምቤላ መሬት ከህወሃት ባለስልጣናት በተጨማሪ፣ ቀድሞ የህወሃት የጦር መኮንኖች በነበሩ ሰዎች ቁጥጥር ስር እንደሚገኝም ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁት ይናገራሉ።

Received on Mon Mar 09 2015 - 16:00:40 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved