Mereja.com: በሽብርተኝነት የተከሰሱ የአየር ኃይል አባላት ነገ ፍ/ቤት ይቀርባሉ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Thu, 18 Jun 2015 23:05:03 +0200

June 18, 2015

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር

ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል የሽብርተኝነት ክስ የቀረበባቸው ሰባት የአየር ኃይል አባላት ነገ ሰኔ 12/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ይቀርባሉ፡፡


አቃቤ ህግ በሰኔ 7/2007 ዓ.ም ባቀረበባቸው ክስ ላይ እንደተመለከተው፣ ተከሳሾቹ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 32(1)(ሀ)ን እና የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 7(1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በሽብተኝነት ተከስሰዋል፡፡ በክሱ የተመለከቱት ተከሳሾች የሚከተሉት ናቸው፣


1ኛ. መ/አ ማስረሻ ሰጤ……አድራሻ ድሬዳዋ
2ኛ. መ/አ ብሩክ አጥናዬ……. ›› ድሬዳዋ
3ኛ. መ/አ ዳንኤል ግርማ…… ›› ድሬዳዋ
4ኛ. ገዛኸኝ ድረስ………. ›› ድሬዳዋ
5ኛ. ተስፋዬ እሸቴ…….. ›› ምስራቅ ጎጃም
6ኛ. ሰይፉ ግርማ……. ›› አዲስ አበባ
7ኛ. የሻምበል አድማው…… ›› ምስራቅ ጎጃም፣ ናቸው፡፡


በአቃቤ ህግ ክስ ላይ እንደተመለከተው ተከሳሾች ‹‹….ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል የማፈራረስ ዓላማ ይዘው ….በሽብር ድርጅት ውስጥ አባል በመሆንና በሽብር ድርጅት ተግባር ላይ ለመሳተፍ በማሰባቸው….›› የሽብርተኝነት ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡


ተከሳሾች ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ አየር ኃይል በመክዳት ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሊያመሩ ሲሉ ባህር ዳር እና ጎንደር ላይ እንደተያዙ በክሳቸው ላይ የተመለከተ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የሽብር ድርጅት አባል በመሆን፣ ተልዕኮ በመቀበል፣ አባላትን በመመልመል እና መረጃ በማቀበል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡


የአየር ኃይል አባላት ተከሳሾቹ በነገው ዕለት አቃቤ ህግ ባቀረበባቸው ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ተከሳሾች ለወራት ከቆዩበት ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ወጥተው በአሁኑ ወቅት ቂሊንጦ እስር ቤት እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Received on Thu Jun 18 2015 - 17:05:04 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved