Ethsat.com: በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት እና የአየር ሃይል የበረራ አስተማሪዎች ታሰሩ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Thu, 16 Apr 2015 17:45:50 +0200

በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት እና የአየር ሃይል የበረራ አስተማሪዎች ታሰሩ

April 15, 2015

ሚያዝያ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን ከፍተኛ የደህንነት ሃላፊዎች  ያስተላለፉትን ድንገተኛ ትእዛዝ ተከትሎ በፌደራል ፖሊስ አባላት የእጅ ስልኮችና የኢሜል አካውንቶች ላይ በተደረገ ፍተሻ፣ የተቃዋሚ መሪ ፎቶዎችን፣ አገራዊ ሙዚቃዎችንና ማንኛውም ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ከኢንተርኔት አውርደው በስልካቸው ላይ ያስቀመጡ ፖሊሶች ተይዘው የተወሰኑት ማእከላዊ ሲገቡ፣ የተወሰኑት ደግሞ ጃንሜዳ አካባቢ በሚገኝ እስር ቤት መታሰራቸውን የፖሊስ ምንጮች ገልጸዋል።

በድንገት የተደረገውን ፍተሻ ተከትሎ በአጠቃላይ ከ120 ያላነሱ ፌደራል ፖሊስ አባላት ሲታሰሩ፣ በፍተሻው በቀጥታ የተቃዋሚ መሪዎች ፎቶዎች ወይም ፖለቲካ ነክ የያዙ ጽሁፎች የተገኙባቸው 37 የሚሆኑ ፖሊሶች ማእከላዊ ተወስደው ታስረዋል።

ከ80 በላይ የሚሆኑት ደግሞ አጠራጣሪ የሆኑ ጉዳዮች አሉ በሚል ለተጨማሪ ምርመራ ጃን ሜዳ አካባቢ በሚገኝ ማቆያ እንዲታሰሩ ተደርጓል።

የፌደራል ፖሊስ አዛዦች የሚሰጡትን ትእዛዝ ላለመቀበል ያንገራግራሉ ተብለው አስቀድመው በተለዩ ፖሊሶች ላይ ደግሞ ክትትሉ መጨመሩን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በዚህም መሰረት በአርማጭሆና ሰሜን ጎንደር የጸረ ሽብር ግብረሃይል ሃላፊዎች የሆኑት ኢንስፔክተር ስንታየሁ፣ ሳጅን አበበ እና ም/ል ሳጅን ብርሃኑ ተይዘው ወደ ማእከላዊ ተወስደዋል።

በእስር ላይ የሚገኙት የግንቦት7 ዋና ጻሃፊ የአቶ አንዳርጋቸውን ፎቶ ግራፍ በብዙ ወታደሮች ሞባይል ስልኮች ላይ መገኘቱን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።

ከድምጻውያን ደግሞ የቴዲ አፍሮ፣ የብርሃኑ ተዘራና የፋሲል ደሞዝ ሙዚቃዎችን ከኢንተርኔት አውርዶ ማዳመጥ ኢህአዴግን እንደመክዳት እያስቆጠረ ነው ተብሏል።

በተመሳሳይ ዜና  ድሬዳዋ ውስጥ በበረራ አስተማሪነት ይሰሩ የነበሩ ሁለት መኮንኖች ሰሞኑን ተይዘው ማእከላዊ መታሰራቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ስማቸውን እስካሁን ለማወቅ ባይቻልም፣ አብራሪዎቹ ቀድም ብሎ ከታሰሩት 4 አብራሪዎች ጋር ግንኙነት ነበራችሁ ተብለው መታሰራቸው ታውቋል።

የኤም 35 ተዋጊ ሄሊኮፕተር የበረራ አስተማሪ የነበረው የሻለቃ አክሊሉ መዘነ ወንድም ሰይፉ መዘነም ማእከላዊ ታስሮ በመሰቃየት ላይ ነው። የቀድሞው አንድነት ፓርቲ የአመራር አባል የነበረው መሳይ ትኩም ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰበት ነው።

ገዢው ፓርቲ በደህንት ተቋማት ላይ ያለው ጥርጣሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍ እያለ መምጣቱን የሚናገሩት ምንጮች፣ ተጨማሪ ፍተሻዎች፣ ድንገተኛ ግምገማዎችና እስሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።

የጥርጣሬው መነሻ ምን እንደሆነ በውል ለማወቅ አልተቻለም። ይሁን እንጅ ስራቸውን እየለቀቁ የሚጠፉ የፌደራል ፖሊሶች ቁጥር መጨመር ስርአቱን ስጋት ላይ ሳይጥለው እንደማይቀር ምንጮች  ይገልጻሉ።

**************************************************************

በሞያሌ በተነሳው ተቃውሞ ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሆቴሎች ከፍተኛ ውድመት ደረሰባቸው

April 15, 2015

ሚያዝያ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የከተማ ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት በከተማዋ ከሚታወቁት  ሆቴሎች መካከል  ፈቃዱ ሆቴል ፣ ኢትዮ ኬኒያ ሆቴል ፣ ሃጎስ ሆቴልና ማሕሌት ሆቴል ጉዳት ድርሶባቸዋል።

የሆቴሉ ባለቤቶች የገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው በሚል ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በተለይ ኢህአዴግን በመደገፍ እና ቅስቀሳ በማድረግ የሚታወቁት የማህሌት ሆቴል ባለቤት ንብረት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።  የአካባቢው ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች የተጎዱ ሆቴሎችን የጎበኙ ሲሆን ፣መረጋጋት እንዲፈጠር ነዋሪዎች ለማሳመን እየጣሩ ነው።

ከሞያሌ ወጣብላ በምትገኘው ኩሌንሳ መንደር የተኩስ ድምጽ መሰማቱን የገለጹት ምንጮች፣ ውጥረቱ አሁንም ድረስ እንዳለ ተናግረዋል። በመከላከያ ሰራዊት አባላትን በሶማሊ ክልል ታጣቂዎች መካከል የተነሳው ግጭት በፌደራል ፖሊሶች ጣልቃ ገብነት ቢበርድም፣ በማንኛውም ጊዜ ሊነሳ ይችላል በሚል ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል። ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና አንዳንድ ድርጅቶች ዛሬ መከፈታቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

Received on Thu Apr 16 2015 - 11:45:50 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved