Ethsat.com: ኢህአዴግ ሰራዊቱን በከፍተኛ ቁጥር ወደ ሰሜን እያጓጓዘ ነው

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 23 Jul 2014 21:32:27 +0200

ኢህአዴግ ሰራዊቱን በከፍተኛ ቁጥር ወደ ሰሜን እያጓጓዘ ነው

23.07.2014

ሐምሌ ፲፮(አስራ ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ የደህንነት አባላት በጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ፣ ኢህአዴግ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሰራዊቱን አባላትና ከባድ መሳሪያዎችን በምሽት ወደ ሽሬ፣ ተከዜ፣ ወልቃይት፣ መተማ፣ አርማጭሆ በመሳሰሉት የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እያጓጓዘ ነው።

ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መታፈን ጋር በተያያዘ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የታው የህዝብ ቁጣ ያስደነገጠው መንግስት፣ ማንኛውም አይነት ተቃውሞ ቢነሳ በሚል ሰራዊቱንና ደህንነቱን እያሰማራ ነው።

ከሰሜን አካባቢዎች የመጡ የደህንነት አባላት፣ ግንቦት7 ከኤርትራ መንግስት ጋር በመተባበር ለአርሶ አደሩ የጦር መሳሪያ በማደል እስከ መሃል አገር ሊገባ ይችላል የሚል አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ ፣ ግንባሩ በድንበር አካባቢዎች ላሰማራቸው የድርጅቱ አባላት ባለሀብቶች ዘመናዊ ስልኮችን በማደል የስለላ ስራ እንዲሰሩ እንዳሰማራቸው ታውቋል።

ከተለያዩ የሰራዊቱ ክፍሎች የሚከዱ ወታደሮች ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ ኢህአዴግ የሚጠፉ ወታደሮችን ለመተካት በሚል ያወጣው የቅጥር ማስታወቂያ የተፈለገውን ያክል የሰው ሃይል አላስገኘለትም።

የኢህአዴግ ሰራዊት በከፍተኛ የሞራል ውድቀት ላይ መሆኑን የሚናገሩት ከሰራዊቱ የሚከዱ ወታደሮች፣ በዘር ላይ የተመሰረተው አደረጃጃት፣ የምግብ አቅርቦት መበላሸት እና የሰራዊቱ የኑሮ ሁኔታ ማሽቆልቆል ለሰራዊቱ ሞራል መውደቅ ዋና ምክንያቶች ሆነው ይጠቀሳሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢህአዴግ የመከፋፈል አደጋ እንዳንዣበበት ምንጮች ገልጸዋል

የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር በተለይ ከአቶ መለስ ሞት በኃላ አገሪትዋን መምራት ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ በዜጎች ላይ የሚወስደው የጅምላ እስርና የማሳደድ ዘመቻ በራሱ አባላት ጭምር ጥያቄ እያስነሳ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

ፓርቲዎች በሽብርተኛነት ሰም ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞች ላይ ያነጣጠረ የእስር እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉ በተለይ መካከለኛና ዝቅተኛ አመራሩ አካባቢ ተቃውሞና ጉምጉምታ እየተሰማ ነው፡፡

ምንጮች እንደገለጹት በኢህአዴግ በኩል የሚወሰደው ኢ-ዴሞክራሲያዊ እርምጃ የህዝብ አመኔታ በማሳጣት የግንባሩን ሕልውና ችግር ላይ ይጥላል የሚሉ እና እየተወሰደ ያለውን ጉልበት የታከለበት እርምጃ በሚደግፉ አባላትና ከፍተኛ ካድሬዎች መካከል መቃቃር እየተፈጠረ መሆኑ ታውቋል፡፡

ግንባሩ በተፈጥሮው ከግምገማ በዘለለ የውስጥ ቅራኔን የሚፈታበት መንገድ የሌለው መሆኑና ልዩነቶች ከባድ ዋጋ የሚያስከፍሉ በመሆናቸው ምክንያት ቅሬታዎቹ ታምቀው እስካሁን መቆየታቸውን የገለጹት ምንጮቻችን በተለይ በሠላማዊ መንገድ ቅሬታውን ከሁለት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ እየገለጸ ያለውን ሰፊ የሙስሊም ማህበረሰብ የተቃውሞ ድምጽ ለማፈን ኃይል የታከለበት ተደጋጋሚ እርምጃ በረመዳን የጾምወርመወሰዱሙስሊም የግንባሩን አባላት ጨምሮ በበርካታ አባላት ዘንድ ተቃውሞ እንዲቀጣጠል ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡

ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከጋዜጠኞች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ አባላት፣ ከሙስሊሙ ህብረተሰብ፣ በብዛት ወጣቶችን ካቀፈው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ማህበረ ቅዱሳን እንዲሁም

በኑሮ ውድነት ከሚሰቃየው ሰፊ ህብረተሰብ እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመላተሙ በመጪው ምርጫ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሊመረጥ እንደማይችል
መገንዘቡን ያስታወሱት ምንጮቹ በዚህ የተነሳ የትኛውንም ዓይነት ተቃውሞ በኃይል ለመደፍጠጥ ወስኖ ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ይህ የግንባሩ እርምጃ ትክክል አይደለም የሚሉ አባላት ብቅ ብቅ ማለታቸው ግንባሩ በቀጣይ ከባድ የመሰነጣጠቅ አደጋ ሊገጥመው እንደሚችል የመጀመሪያው ምልክት መሆኑን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡

 

Received on Wed Jul 23 2014 - 15:33:41 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved