TGindex.blogspot.de: ታሪክ የአሸናፊዎች ነው

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Sun, 28 Dec 2014 21:30:53 +0100
ታሪክ የአሸናፊዎች ነው
ከተስፋዬ ገብረአብ (Gadaa)
28.12.2014
 
“ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” በሚል ርእስ የተፃፈውን የጄኔራል ውበቱ ፀጋዬን መፅሃፍ እያነበብኩ ነው። ከኤርትራ ነፃነት ወዲህ ኢትዮጵያውያን ኤርትራን የተመለከተ መፅሃፍ ሲፅፉ ይህ 28ኛው መሆኑ ነው። በዘውዴ ረታ የተጀመረው፣ ውበቱ ፀጋዬ ላይ አድርሶናል። ወደፊትም ኤርትራን በተመለከተ በየአመቱ ቢያንስ አንድ መፅሃፍ እንደሚፃፍ መገመት ይቻላል። ምክንያቱም ሊፃፍ ከሚገባው የኤርትራ የጦርነትና የፖለቲካ ታሪክ አንድ አምስተኛው እንኳ ገና አልተነካም።
 
የጄኔራል ውበቱን መፅሃፍ ገና አንብቤ አልጨረስኩም። ስጨርስ የተሟላ አስተያየት እፅፍበት ይሆናል። ለዛሬው ግን አንድ ሁለት ነጥቦችን ብቻ በጨረፍታ ላነሳ ወደድኩ።
ጄኔራል ውበቱ በመፅሃፉ መግቢያ ላይ “የኢትዮጵያ ሰራዊት በሻእቢያ ተዋጊዎች ለምን ተሸነፈ?” ለሚለው ጥያቄ ጥቂት ምክንያቶችን አስቀምጦአል። የመልከአምድር አቀማመጥ፣ ወታደሩ በቂ የተራራ ስልጠና አለማግኘት ወዘተ የመሳሰሉት አነስተኛ ምክንያቶች ናቸው። ዋናው ምክንያት ተብሎ የተቀመጠው ግን፣ “የምንዋጋው የህዝብ ድጋፍ ከነበረው ጠላት ጋር በመሆኑ...” የሚለው ነበር። (ገፅ 9) አያይዞም፣ የኤርትራ ህዝብ በጥቅሉ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ የነበሩ ኤርትራውያን ከፍተኛ መኮንኖች ለሻእቢያ መረጃ ያቀብሉ እንደነበር ጠቅሶአል። ገበሬዎች ሳይቀሩ ሰራዊቱን በተሳሳተ መንገድ እየመሩ ለሻእቢያ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ያስደመስሱት እንደነበር ዘርዝሮአል።
 
ጄኔራል ውበቱ እውነት ብሎአል። ለዚህም ይመስላል እንደ ቀድሞው አጠራር የሻእቢያን ታጋዮች “ወንበዴዎች” ብሎ ለመጥራት አልፈለገም። “ተገንጣዮች” የሚል ቃል መጠቀሙን መርጦአል። ግዙፉን የደርግ ጦር አሸንፎ መንግስት ለመመስረት የበቃን ሃይል፣ “ወንበዴ” ማለት ከብዶትም ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ውበቱ  ለ15 አመታት ኤርትራ መሬት ላይ ሲዋጋ የተጠቀመበትን ቃል ለመተው መወሰኑ ያስመሰግነዋል።
 
በሰላሳ አመቱ የጦርነት ዘመን ኤርትራውያን የነፃነት ትግሉ ደጋፊ በመሆን ለአማፅያኑ መረጃ ማቀበላቸውና  ገንዘብ እያዋጡ በምስጢር ወደ በረሃ መላካቸው እውነት ነው። ጄኔራል ውበቱ አላጋነነም። ሌላው ቀርቶ የጄኔራል ውበቱ የቅርብ የስራ ባልደረባ የነበረው ኮሎኔል እዮብ ገብረአምላክ ከስብሃት ኤፍሬም (ጄኔራል) ጋር ግንኙነት ፈጥሮ፣ የሰራዊቱን እቅዶች በሙሉ ለሻእቢያ ይልክ ነበር። (የስደተኛው ማስታወሻ - ገፅ 205) ርግጥ ነው፣ የመረጃ የበላይነት ያለው የማሸነፍ እድሉ ጠንካራ ነው።
 
ከጄኔራል ውበቱ መፅሃፍ በሁለተኛ ደረጃ የገረመኝ ነጥብም አለ።
የመፅሃፉ ምእራፍ ሁለት ከዋቆ ጉቱ ጋር የተደረገውን ጦርነት የሚዘግብ ነው። ውበቱ ፀጋዬ ወጣት ሻምበል ሳለ የዘመቻ መኮንን ሆኖ ባሌ ላይ በተደረገው ውጊያ ላይ መሳተፉን ዘግቦአል። በዋቆ ጉቱ እየተመሩ ባሌ ላይ ያመፁትን ኦሮሞ ገበሬዎች ጄኔራል ውበቱ፣ “ወንበዴዎች” እያለ ነበር የሚገልፃቸው። እዚህ ላይ ስደርስ ከፍ ባለ ድምፅ ስቄያለሁ። ሻእቢያ ስላሸነፈ ወንበዴነቱ ተሰረዘለት። ዋቆ ጉቱ ስላልተሳካለት ወንበዴነቱ ፀድቆ ቀረ። ዋቆ ጉቱ ቢሳካለት ኖሮ እንደ ጆሞ ኬንያታ ወይም በሳሞራ ማሼል ደረጃ ስሙ በተጠራ ነበር። ወንበዴነቱም በተሰረዘለት። ጄኔራል ውበቱ ስለ ዋቆ ጉቱ ምን ያህል እንደሚያውቅ አላውቅም። ስሙን እንኳ አስተካክሎ አልፃፈም። “ዋቆ ጉቶ” እያለ ነበር ያሰፈረው። ለመሳደብ ፈልጎ ይሁን የታይፕ ስህተት አላውቅም። ያም ሆነ ይህ ዋቆ ጉቱ ፍትሃዊ ጥያቄ ነበር ያነሳው። ሁዋላ ደርግ አጥጋቢ ምላሽ የሰጠበትን የቀላድና የገባር የመሬት ስርአትን ነበር የተቃወመው። ዋቆ ጉቱ የኦሮሚያን የመገንጠል ጥያቄ እንኳ ያነሳ አይመስለኝም። ጄኔራል ውበቱ ሻእቢያን “ወንበዴ” ለማለት ተሳቆ፣ የዋቆ ጉቱን ተከታዮች “ወንበዴዎች” ለማለት መድፈሩ ስላቅ ነበር የሆነብኝ። እና “ታሪክ የአሸናፊዎች ነው” የሚለውን አባባል ለማስታወስ ተገደድኩ።
 
ከኦሮሞ ወዳጆቼ ጋር ስንጨዋወት ብዙ ጊዜ የማነሳው አንድ ነጥብ አለ። በአፍሪቃ ቀንድ ባህልና ልማድ ክብር ለማግኘት የግድ ሃይል ያስፈልጋል። ሃይል ከሌለ ክብር የለም። ክብር ከሌለ ህይወት የለም። በአካባቢያችን በልመና ወይም በድርድር ክብርና ነፃነትን ማግኘት ህልም ነው። ማንዴላ ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ ገድለን ቀብረነው ነበር። ስለዚህ በማንዴላ መንገድ ክብር ለማግኘት መሞከር የዋህነት ነው።
 
ጄኔራል ውበቱ የፖለቲካ ሰው አለመሆኑ በርግጥ ካልተደራጀውና በተቃርኖ ከተሞላው ፅሁፉ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።ለመጥቀስ ያህል “ሻእቢያ ሙሉ የህዝብ ድጋፍ ነበረው” ብሎ ሲያበቃ፣ እልፍ ብሎ ደግሞ፣ “በኤርትራ ውስጥ ለአንድነት ሲባል ለ30 አመታት የተደረገው ጦርነት” እያለ ይቀጥላል።
 
የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር አንድነት አለመፈለጉን ጄኔራል ውበቱ ካመነ፣ ኢትዮጵያ ያደረገችው ጦርነት ለአንድነት ሳይሆን ለወደብና ለመሬት ነበር ማለት ነው። ምክንያቱም “አንድነት” የሚለው ቃል ሰዎችን እንጂ መሬትን የሚመለከት አይመስለኝም። ዛሬም ድረስ አንዳንድ ፖለቲከኞች “ትግራይ ከፈለገች ትገንጠል። ድንጋይ ናት።” ሲሉ ይሰማሉ። የኦሮሚያና የኤርትራ ጉዳይ ሲነሳ ወደብና ቡናውን በማስታወስ ይንገበገባሉ። ህዝቡን ንቆ መሬት ለመያዝ የሚሞክር መቼም ቢሆን አይሳካለትም።
 
ጄኔራል ውበቱ ፀጋዬ የጦርሜዳ ልምዱን በመፃፉ ሊመሰገን ይገባዋል። ግልፅነቱ አያስወቅሰውም። ካልፃፉት እሱ ይሻላል። በኤርትራ ቆይታው የኤርትራ ህዝብ ላይ ጥላቻ እንዳልነበረው፣ በጥቅሉ ፕሮፌሽናል ወታደር እንደነበር በቅርብ የሚያውቁት ነግረውኛል። በድጋሚ ባርኔጣዬን አነሳለታለሁ።
 
Received on Sun Dec 28 2014 - 15:30:55 EST

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved