[dehai-news] Goolgule.com: 1. የቢሮ ኃላፊው በሙስና ላይ ምስክር ሳይሆኑ ተገደሉ 2. የሙስና ምርመራ እየተወሳሰበ ነው!-"መበላላት እንዳይጀመር ስጋት አለ"

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 18 Jun 2013 12:51:59 +0200


የቢሮ ኃላፊው በሙስና ላይ ምስክር ሳይሆኑ ተገደሉ


“ብዙ ሳይታወቅ የተገደሉ ተስፋዬዎች አሉ”

 

June 17, 2013 07:55 am By Editor <http://www.goolgule.com/author/hakimy/> 3 Comments <http://www.goolgule.com/tesfaye-murdered/#comments>

በነበራቸው የስራ ሃላፊነት በድብቅ መረጃ ሲያሰባስቡ ቆይተው ለመንግስት ካጋለጡ በኋላ ራሳቸውን ደብቀው የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኢሬሣ ምሳ እየተመገቡ ህይወታቸው ማለፉ ተሰማ። አቶ ተስፋዬ ሰኞ ለጸረ ሙስና ኮሚሽን የምስክርነት ቃላቸውን ለመስጠት ከኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ጋር ቀጠሮ ይዘው ነበር።

በቅርቡ ወደ ፌደራል መንግስት የተዛወሩት የጋምቤላ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኡሞት ኦባንግ፣ ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ አላግባብ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን፣ እንዲሁም በክልሉ የሚፈጸሙትን የተጭበረበሩ የበጀት አፈጻጸሞችንና ምዝበራዎችን የሚያጋልጡ ሰነዶችን በሚስጥር በማደራጀት ለኢህአዴግ ያቀረቡት አቶ ተስፋዬ አሟሟታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

አቶ ተስፋዬ ኢሬሳ ከፍተኛ ምስጢር ያላቸውን ሰነዶች በመያዝ ከመታሰራቸው በፊት መሰወራቸውን፤ “የቢሮ ሃላፊው ይዘው የተሰወሩት መረጃ አቶ ኦሞት የፈረሙባቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሰነዶችና ሙስና የተከናወነባቸው የኮንስትራክሽንና የተለያዩ መረጃዎች ናቸው። መረጃዎቹ አንድ ቀን ህዝብ ፍርዱን ይሰጥ ዘንድ ይፋ ይሆናሉ” በሚል <http://www.goolgule.com/corruption-in-gambella/> ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ በ (ጥቅምት 19፤2005/October 29, 2012) መዘገቡ ይታወሳል።

ቀደም ሲል የጋምቤላ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ከላይ የተጠቀሰውን የሙስና ወንጀል በማጋለጣቸው ጋምቤላ መኖር ሳይችሉ ቀርተው ራሳቸውን ሸሽገው ለመኖር ተገደው እንደነበር የሚያውቋቸው ለጎልጉል አስረድተዋል።
“አቶ ተስፋዬ ሙስናን በማጋለጣቸው በፍርሃቻ ራሳቸውን ደብቀው ሊኖሩ አይገባም” በማለት ኢህአዴግ ከለላ እንደሚሰጣቸው ቃል በገባላቸው መሰረት ከተሸሸጉበት የወጡት አቶ ተስፋዬ ሰንጋተራ ትንሳዔ ሆቴል ከጋምቤላ ልጆች ጋር መገናኘት ይጀምራሉ።

ባለፈው ሳምንት ከፌዴራል የጸረ ሙስና ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ከያዙ በኋላ ኮሚሽነሩ በድንገት ለለቅሶ ወደ ጎንደር በመሄዳቸው ቀጠሮው ለሳምንት ይራዘማል። ለሰኞ (ሰኔ10፤2005) አዲስ ቀጠሮ ይይዛሉ።

በስልክ ያነጋገርናቸው ትንሳዔ ሆቴል አካባቢ እንደነበሩና ለጉዳዩ ቅርበት እንዳላቸው የሚገልጹ የጋምቤላ ተወላጅ የስራ ሃላፊ እንዳሉት አቶ ኦሞት ኦባንግ ለአቶ ተስፋዬ ስልክ ደውለው ነበር። አቶ ተስፋዬ ህይወታቸው ከማለፉ ሁለት ቀን በፊት የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኦሞት በስልክ ተማጽንዖ አቅርበው ነበር።

አቶ ኦሞት “እውነት ነው ጸረ ሙስና ኮሚሽን ቀጠሮ የያዝከው?” በማለት ይጠይቃሉ

“አዎ! እውነት ነው” በማለት አቶ ተስፋዬ መልስ ይሰጣሉ።

አቶ ኦሞት መልሰው “እንግዲያውስ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከመግባትህና ከማነጋገርህ በፊት ሁለታችን መገናኘት አለብን። የምንነጋገረው ነገር አለ” የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ። አቶ ተስፋዬ ስለ ስልክ ልውውጡ እንደነገሯቸው የተናገሩት እኚሁ ሰው፣ አቶ ኦሞት በስልክ ደጋግመው በመደወል ያቀረቡትን የ”እንነጋገር” ጥያቄ አቶ ተስፋዬ አልቀበልም ይላሉ።

ጋምቤላ ስራቸውን ለቀው ራሳቸውን ደብቀው የኖሩት በእርሳቸው ምክንያት መሆኑን፣ ፍትህ እንደሚፈልጉ፣ አሁን ለመነጋገር ጊዜው እንዳልሆነ፣ ዘርዝረው ለአቶ ኦሞት መናገራቸውን ያወሱት የ <http://www.goolgule.com/tesfaye-murdered> ጎልጉል ምንጭ፣ ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው አቶ ኦሞት በንዴት ተዛልፈው ነበር።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ አቶ ተስፋዬ ትንሳዔ ሆቴል ሰዎችን በመላላክና በመታዘዝ ከሚኖር አንድ የጋምቤላ ሰው /አቶ ተስፋዬ የሚረዱት በምግባር ጉዳይ የሚታማና ጸበኛ የሚባል ሰው ነው/ አብረው ተቀምጠው ምሳ እየበሉ ሳለ አቶ ተስፋዬ አረፋ ይደፍቃቸዋል። ወዲያው ከተቀመጡበት ተንሸራተው መሬት ይወድቃሉ። ቀጥሎም ሰውነታቸው ይዝልና ኮማ ውስጥ ይገባሉ። ከአፋቸው እየተዝለገለገ የሚወጣው ፈሳሽ በመጨመሩና የተለያየ ርዳታ ቢደረግላቸውም ሊተርፉ ስላልቻሉ ሆስፒታል ተወስደው ህይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል።

አቶ ተስፋዬ ሆስፒታል ከመድረሳቸው በፊት እንደሞቱ የሚናገሩት የጎልጉል ምንጭ አሟሟታቸው ከመርዝ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ተስፋዬ በሙስና ወንጀል ላይ ያሰባሱትን መረጃ ለተለያዩ አካላት የበተኑ ስለሆነ እሳቸውን በመግደል ማድበስበስ እንደማይቻል አስታውቀዋል። አቶ ተስፋዬ ሙስና ካጋለጡ በኋላ መሰወራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው። በተያያዘ በጋምቤላ ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ውስጥ ከ70በመቶ በላይ የሆኑት የህወሓት የቀድሞ ታጋዮች የነበሩና የክልል አንድ ተወላጆች መሆናቸው የአቶ ተስፋዬን አሟሟት ይበልጥ ውስብስብ እንዳደረገው አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ “የአቶ ተስፋዬ ሞት አሳዛኝና አስደንጋጭ ነው። ብዙ ሳይታወቅ የተገደሉ ተስፋዬዎች አሉ” በማለት ስለ አቶ ተስፋዬ ሞትና አሟሟት መረጃ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።

“አቶ ተስፋዬ ለእውነት ሲል ሞቷል። ኢህአዴግ ውስጥ በርካታ የወንጀል መረጃ ያላቸው ወገኖች አሉ። እንዲህ ያሉ ዜጎች በየትኛውም ዘመን አይረሱም። የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ስማቸውና ታሪካቸው ከጨዋነታቸው ጋር ተመልሶ ህያው ይሆናል። ሌቦችና ነፍሰገዳዮች ወደ ህግ ሲያመሩ፣ እንደ አቶ ተስፋዬ አይነቶቹ የመጪው ትውልድ ታላቅ ምሳሌ ሆነው እየተወደሱ ህያው ሆነው ይኖራሉ” የሚል አስተያየት የሰጡት አቶ ኦባንግ፤ አቶ ተስፋዬ ያሰባሰቧቸው የሙስናና ተመሳሳይ ወንጀሎች ማሳያ ሰነዶች እጃቸው ላይ ስላለ አቶ ተስፋዬን በመግደልና በማስገደል ወንጀል ማድበስበስ እንደማይቻል ተናግረዋል።

የአቶ ተስፋዬ የቀብር ስነስርዓት ጋምቤላ መፈጸሙን ለመረዳት ተችሏል። ቤተሰቦቻቸውን በማግኘት ሆስፒታሉ ስለ አሟሟታቸው የሰጠውን አስተያየት ጠይቀን ለመረዳት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም።

************************************************************************************************************************************************


የሙስና ምርመራ እየተወሳሰበ ነው!


"መበላላት እንዳይጀመር ስጋት አለ"

 

June 18, 2013 08:08 am By <http://www.goolgule.com/author/hakimy/> Editor <http://www.goolgule.com/corruption-crime-complicated/#comments> Leave a Comment

በጉምሩክና ገቢዎች ባለስልጣን የተጀመረው የጸረ ሙስና ዘመቻ ተከትሎ እየተካሄደ ያለው ምርመራ እየተወሳሰበ መሔዱ ተሰማ። በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ተከሳሾች የሚሰጡት መረጃ መበላላት ያስነሳል የሚል ፍርሃቻ እያስነሳ ነው። “ሰፈር የለየው” የጸረ ሙስና ዘመቻ የፈጠረው ስጋት የሃይል ሚዛን የያዙትንም ስጋት ውስጥ ከትቷል።

በኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ የታየው የውስን ሰዎች በድንገት በመበልጸግ ከባለስልጣኖችና ከከፍተኛ የስርዓቱ ሰዎች ቤተሰቦች ጋር በሚከናወን መተሳሰር አማካይነት እንደሆነ ከህዝብ የተሰወረ አይደለም። ሰሞኑንን ይፋ የተደረገው የባንክና የንብረት እግድ እንዳመለከተው የዝርፊያው ሰንሰለት በቤተሰብ የታጠረ መሆኑን ነው።

አቶ መለስ ከድነው ያቆዩትና የሳቸውን ሞት ተከትሎ ከፖለቲካው ልዩነት ጋር በተያያዘ እንደተጀመረ የሚነገርለት የጸረ ሙስና ዘመቻ፣ በመንግስት በኩል “ቆራጥ” አቋም የተያዘበት እንደሆነ ቢነገርም አስጊ ሁኔታ እየተፈጠረ ስለመሆኑ <http://www.goolgule.com/corruption-crime-complicated/> የጎልጉል የጸረ ሙስና ኮሚሽን ምንጮች ይናገራሉ።

እየተካሄደ ካለው ምርመራ በተገኙ ጭብጦች መታሰር የሚገባቸው ባለስልጣናት እንዳሉ የሚጠቁሙት እነዚሁ ክፍሎች፣ ምርመራው እየሰፋና እየጠለቀ ሲሄድ ችግር ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩን አይሸሽጉም።

“የመጨረሻው መጠፋፋት መጀመሪያ ላይ እንዳሉ የሚሰማቸው አሉ” በማለት <http://www.goolgule.com/corruption-crime-complicated/> ለጎልጉል መረጃ የሰጡት ክፍሎች “እየሰፋ የሄደውንና መጨረሻው ወዴት እንደሚያመራ የሚታወቀውን የጸረ ሙስና ዘመቻ የማስቆም ፍላጎት እንዳለ የሚያመላክቱ ሁኔታዎች በቢሮ ደረጃ እየሰማን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ዘመቻው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት የሚሉ ክፍሎች ስላሉ በሙስና የሚጠረጠሩ ፕሮጀክቶችና ከፍተኛ ግንባታዎችን አስመልክቶ በስፋት መረጃ የሚደርሰው ኮሚሽኑ፣ ከነገ ዛሬ ይመጣብናል በሚል የተፈጠረው መደናገጥ በህገወጥ ሃብት የሰበሰቡትን በሙሉ ስጋት ላይ ጥሏቸዋል። በባንኮች አካባቢ ገንዘብ የማሸሽ፣ ከዶላር ገበያ ራስን የማግለልና የሃይል ሚዛን በመመልከት የመተጣጠፍ ሩጫ በስፋት እንደሚስተዋል <http://www.goolgule.com/corruption-crime-complicated/> የጎልጉል ሰዎች ተናግረዋል።

በሙስናው ሰለባ የሆኑት ቡድኖች አቅማቸውና ትስስራቸው ቀላል ባለመሆኑ፣ የታጠቁ ሃይሎችም ስላሉበት የርስ በርስ መተላለቅ ሊከተል ይችላል በሚል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ያመለከቱት <http://www.goolgule.com/corruption-crime-complicated/> ምንጮች “አቶ መለስ የዘረጉትን ሰንሰለት ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ችግር እየታየ ነው። መተላለቁ በዚህ ክፍተት ውስጥ ሊከሰት ይችላል” የሚል ስጋት መንገሱን አመልክተዋል።

የሚታወቁ ባለስልጣናትና የክልል አመራሮች “ልማታዊ” ከሚባሉት ኢህአዴግ ሰራሽ ባለሃብቶች ጀርባ ሆነው ፕሮጀክትና ጨረታ በማጸደቅ ምዝበራውን እንደሚመሩ መረጃ ስለመኖሩ የሚናገሩት <http://www.goolgule.com/corruption-crime-complicated/> ምንጮች፣ “በቅርብ ተመስርተው ከፍተኛ ሃብት በሰበሰቡ ሪል ስቴት፣ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች፣ አስመጪና ላኪዎች፣ ሰፋፊ መሬት ለአረብ አገር ባለሃብቶች በማስማማት አየር በአየር የሚጫወቱ፣ በአገሪቱ ከሚታዩት ታላላቅ ግንባታዎች ጋር በተያያዘ ወዘተ ዋናዎቹ ባለስልጣኖችና ቤተሰቦቻቸው ተዋናይ መሆናቸው ይታወቃል። የህወሃት ሰዎች ግንባር ቀደም ናቸው” በማለት የስጋቱን መጠን ይገልጻሉ።

ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በአፍሪካና በተለያዩ አገራት የሽርክና ንግድ የከፈቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዳሉ የሚገልጹት የኢህአዴግ የቅርብ ሰዎች “አሁን አመራር ላይ ያሉት የህወሃት ሰዎች የእነዚህን ባለስልጣናት በቤተሰብና ከፍተኛ አቋም በገነቡ ድርጅቶች አማካይነት የተበተቡት ሰንሰለት በቀላሉ መበጠስ ስለማይችሉ የሙስናው ዘመቻ አደጋ ይገጥመዋል። አለያም እርስ በርስ መበታበት ሊከተል ይችላል” በሚል ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቀረጥ ነጻ በማስገባት ከፍተኛ የመንግስት ገቢ ለግል ተጠቅመዋል በሚል በተከሰሱት ሰዎች ላይ እየተካሄደ ባለው ምርመራ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በከፍተኛ ባለስልጣናት ትዕዛዝ አማካይነት የቀረጥ ነጻ ፈቃድ መስጠታቸውን ለምርመራ መኮንኖች መናገራቸውን <http://www.goolgule.com/corruption-crime-complicated/> የጎልጉል ምንጮች አመልክተዋል።

በዚህም የተነሳ ሸራተንን ተገን ያደረጉት የባለሃብቱ ወኪል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቃቸው ተሰምቷል። በነባር የህወሃት ሰዎች የማይወደዱት እኚሁ የባለሃብቱ ወኪል፣ ወ/ሮ አዜብን፣ አቶ አዲሱ ለገሰና የባለሃብቱ ዋና ሸሪክ የሆኑትን አቶ በረከትን ቢተማመኑም ምርመራው ወደእርሳቸው ሊሄድ እንደሚችል <http://www.goolgule.com/corruption-crime-complicated/> የጎልጉል ምንጮች ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል። አንዳንዶቹ የቀድሞ ሸሪኮቻቸው ስልካቸውን ስለማያነሱላቸው ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውና ከወትሮው የተለየ ያለመረጋጋት እንደሚታይባቸው የቅርብ ሰዎቻቸውን ሳይቀር ሰላም እንደነሳ ለማወቅ መቻላቸውንም ተናግረዋል።

አብዛኛውን የንግድ በሮች በስጋ ዘመዶቻቸውና በአገር ልጆች ተብትበው የያዙት የባለሃብቱ የኢትዮጵያ ወኪል ምርመራ ዙሪያ የሚነሱትን ጉዳዮች ከመጥቀስ የተቆጠቡት ምንጮች፣ በቅርቡ አዲስ ነገር እንደሚሰማ መረጃዎች እንዳሏቸው አመልክተዋል። ለሸራተኑ ሰውና ለሸራተኑ ቡድኖች እጅግ ቅርብ ነን የሚሉ በበኩላቸው “ወ/ሮ አዜብ መስፍንና አቶ አዲሱ ለገሰ እስካልተነኩ ድረስ ሸራተን ሰላም ነው። አቶ ጌታቸውም እዛው ናቸው” ሲሉ የለበጣ ቀልድ ቀልደዋል። እነዚሁ ክፍሎች ቢያንስ “የኤች አይ ቪ/ኤድስ እድሜ ማራዘሚያ እናመርታለን፣ ለወገን እንደርሳለን በሚል ሰበብ በከፍተኛ ማጭበርበር የተፈጸመውን ወንጀል ጉዳይ ዝም አይበሉት” ሲሉ ለጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ አደራቸውን አስተላልፈዋል።

 

Received on Tue Jun 18 2013 - 08:53:08 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved